News Detail
Oct 30, 2020
755 views
የመምህርነት ሙያ ከዘር፣ ከብሄርና ከወገንተኝነት ነፃ ሆኖ በከፍታ ላይ የሚገኝ ግዙፍ ሙያ ነው:- ጌታሁን መኩሪያ (ፒ ኤች ዲ) የትምህርት ሚኒስትር
"መምህራን ቀውስ ለመቀልበስም ሆነ ለመጪው ጊዜ ብሩህነት ግንባር ቀደም ሚና አላቸው" በሚል ትምህርት ሚኒስቴር ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር ያዘጋጁት የመምህራን ቀን ዓመታዊ በዓል አውደ ጥናት በባህር ዳር እየተካሄደ ነው።
የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ፒ ኤች ዲ) አሁን እየታዩ ያሉ ሀገራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ግብረገብነት ያለው፣ ብዝሃነትንና አንድነትን የሚያስተናግድ ትውልድ ለማፍራት እንደሚሰራ አንስተዋል።
የያዘነው የትምህርት ሙያ ከዘር፣ ከብሄርና ከወገንተኝነት ነፃ ሆኖ ከፍ ብሎ የሚገኝ ግዙፍ ሙያ ነው ነው ያሉት ሚኒስትሩ ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ መምህራን ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።
ሁላችንም የመምህራን የእጅ ስራ ውጤት ነን ያሉት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የሰራተኛ ጉዳይ ሃላፊ ሙሉነሽ አበበ (ፒ ኤች ዲ) የመምህራን ክብር በሚከፈሉት ክፍያና በሚኖሩት ኑሮ የሚለካ ሳይሆን ሙያው በራሱ ክቡር የሚሰጠው ነው ብለዋል።
የትምህርት ዘርፉ ለሀገር እንዲጠቅም ለማድረግም የመምህራንን ጥቅም ማስጠበቅ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።
የመምህራን ቀን በሁሉም ክልሎች በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ሲሆን የማጠቃለያ ዝግጅቱ ደግሞ በአዲስ አበባ ይደረጋል።
በዓውደ ጥናቱ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የሰው ሃብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ሰብሳቢ ወ/ሮ እምየ ቢተውን ጨምሮ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የአማራ ክልል፣ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የመምህራን ማህበር ሃላፊዎች ተሳታፊ ናቸው።