News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Mar 10, 2022 1.2K views

የትምህርት ቤት ምገባ የትምህርት ተደራሽነትንና ጥራትን ለማሳደግ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተገለፀ ።

የትምህርት ቤት ምገባ ቀን በአፍሪካ ለ7ኛ በአገራችን ለ4ኛ ጊዜ "የተጠናከረ የመዋዕለ-ንዋይ ፍሰት በአገር በቀል የትምህርት ቤት ምገባ፤ ለአፍሪካ የሥርዓተ-ምግብና ሰብዓዊ ልማት!” በሚል መሪ ቃል በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልል በፊንፊኔ ልዩ ዞን በጫንጮ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከበረ።
በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ቤት መሻሻል ፕሮግራም ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ዮሐንስ ወጋሶ የትምህርት ቤቶች ምገባ መርሃ ግብር ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡና ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ ለማድረግ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልፀዋል።
ከዚህም ባሻገር የምገባ መርሃ ግብሩ የትምህርት ተደራሽነትንና ጥራትን ለማሳደግ ጉልህ ድርሻ እንዳለውም ዳይሬክተር ጄኔራሉ አክለው ተናግረዋል፡፡
መንግሥት ለመርሃ ግብሩ ትኩረት በመስጠት 2.7 ቢሊዮን ብር በላይ በመመደብ 1.3 ሚሊዮን ያላነሱ የቅድመ አንደኛና የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መርሃ-ግብሩ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ከማድረግ በተጨማሪ ለአካባቢው አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር በመፍጠር ገበያ ተኮር የማምረት ዘይቤን እንዲከተሉ እንደሚያደርግም ተገልጿል።
በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል መንግሥት የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቶላ በሪሶ(ዶ/ር) መርሐ-ግብሩ በኦሮሚያ ክልል በ2007ዓ.ም የተጀመረ መሆኑን ጠቀሰው በየአመቱ የትምህርት ቤት ምገባ በጀት በመጨመር መርሃ ግብሩ በተጠናከረ ሁኔታ እየተተገበረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ ልዩ ዞን የሚገኙ ተማሪዎች የምገባው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር ጋር በቅንጅት ሥራ መጀመራቸውንም ሃላፊወ ተናግረዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ የጸደቀውን የትምህርት ቤቶች ምገባ የፖሊሲ ማዕቀፍና ማስፈፀሚያ ስትራቴጂን መሠረት በማድረግ በቀጣይ ሁሉም ሕፃናት የትምህርት ቤቶች ምገባ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራም ተጠቅሷል።
Recent News
Follow Us