News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Oct 06, 2021 615 views

የትምህርት ሚኒስቴር በአማራ ክልል በህወሃት የሽብር ቡድን ጉዳት ለደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች የ100 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ።

የትምህርት ሚኒስቴር በአማራ ክልል በሽርተኛው የህወሃት ቡድን ለወደሙና ለፈረሱ ትምህርት ቤቶች መልሶ ማቋቋሚያ የሚሆን የ100 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረጓል።
በትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ( ዶ/ር ኢንጂ. ) የተመራው የልዑካን ቡድን ድጋፉን ለክልሉ አስረክቧል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ይልቃል ከፋለ (ፒ ኤች ዲ) የህወሃት የሽብር ቡድን በፈፀመው ጥቃት በክልሉ 2ሺ 903 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ የወደሙ ሲሆን ከ1.5 ሚሊየን በላይ ህፃናት ደግሞ ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ( ዶ/ር ኢንጂ ) አሸባሪ ቡድኑ ጦርነት መክፈቱ ሳያንስ የትምህርት ተቋማትን በማውደም የድንቁርናውን ጥግ አሳይቷል ብለዋል።
እንደ ትምህርት ሚኒስቴር ሌሎች ክልሎች ላይ ያሉ ህፃናት ወደ ትምህርት ቤት ለመግባት በሚጓጉበት በዚህ ሰዓት፤ በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ ህፃናት በሶቆቃ፣ በርሃብ፣ ቤተሰባቸውን በሞት አጥተው ወይም ቆስለውባቸው መሰቃየታቸውን ስናስብ እጅግ ያስዝነናል ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው ይህ ሽብርተኛ ቡድን በክልሉ በገባባቸው አካባቢዎች የመንግስት ተቋማትን፣ትምህርት ቤቶችና ጤና ተቋማትን፣ የጦር ካምፕ በማድረግ ፣ በመዝረፍ እንዲሁም የተቀረውን በማውደም ለህዝብ ያለውን ጥላቻ በግልጽ አሳይቷል ብለዋል፡፡
ክልሉ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባትና ለማቋቋም ለሚያደርገው ጥረት የትምህርት ሚኒስቴር ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር የህወሃት የሽብር ቡድን ጉዳት ባደረሰባቸው አካባቢዎች አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
Recent News
Follow Us