News Detail
Aug 20, 2020
1.1K views
የአንድነት ፓርክና የእንጦጦ ፕሮጀክቶች ትልቅ ማሰብ፣ ማቀድና በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅን የተማርንባቸው ናቸው፡-ትምህርት ሚኒስቴር
የትምህርት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች የሸገር ፕሮጀክትንና እንጦጦ ፓርክን ጎብኝተዋል፡፡
የጉብኝቱ ዋነኛ አላማም በሀገራችን በርካታ ስራዎችን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ለማሳየትና በአመራሩና ሰራተኞች ዘንድ መነቃቃትን ለመፍጠር መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ ገልፀዋል፡፡
ይህ ፕሮጀከት እንደ አጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ትልቅ ነገር በማሰብ በአጭር ጊዜ በጥራትና በብቃት ማጠናቀቅ እንደሚቻል የተማርንበት ፕሮጀክት ነው ብለዋል ፡፡
በተጨማሪም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በበላይነት መርተው ይህንን የመሰለ ስራ መስራት ከቻሉ እኛም ከዚህ ፕሮጀክት ትምህርት ወስደን በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፉ ከ45ሺ በላይ የትምህርት ተቋማት ገጽታ መቀየር ብንችል ሀገር መቀየር እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስር በየደረጃው ያሉ አመራሮችና ሰራተኞች ይህንን መነቃቃት በውስጣቸው በመፍጠር ከተለመደው አሰራር በመውጣት በስራቸው ያሉትን የትምህርት አመራሮችን፣ መምህራንና ተማሪዎችን እንዲሁም ተቋማትን በማስተባበር ዘመኑን የሚመጥን ስራ በመስራት ኋላፊነታቸውን እንዲወጡ ክቡር ሚኒስትሩ በጉብኝቱ ወቅት አሳስበዋል ፡፡
በመጨረሻም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አመራሮችና ሰራተኞች በእንጦጦ ፓርክ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አከናውነዋል፡፡