News Detail

National News
Sep 16, 2025 20 views

ተቋማት ከተልዕኳቸው አንጻር ተገቢነት ባላቸው የትምህርት መስኮች ብቻ ላይ ትኩረት አድርገው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተጠቆመ፤ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ "በአዲስ ምዕራፍ ዋዜማ" በሚል መሪ ቃል ዩኒቨርሲቲውን በአዲስ የማደራጀት ሪፎርም ማስጀመሪያ ውይይት አካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የኢትዮጵያ ሰቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የህብረተሰቡን ወቅታዊና የመጪውን ጊዜ ፍላጎት ማሟላት የሚችሉ ብቃትና ጥሩ ሥነ-ምግባር የተላበሱ የህዝብ አገልጋዮችን ማፍራት እንዲችል ከተልዕኮው አንጻር ተገቢነት ባላቸው የትምህርት መስኮች ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እየተተገበረ ያለውን ሀገራዊ የሪፎርም ሥራ መሸከም የሚችል ተቋምና ሲቪል ሰርቫንት ለማፍራት በሚያስችል መልኩ እራሱን መልሶ ማደራጀት እንደሚገባው ጠቁመዋል።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ አክለውም ዩኒቨርሲቲው ኢትዮጵያ በምትፈልገው የዕድገትና የስልጣኔ ደረጃ ላይ ማድረስ የሚያስችል የመንግሥት አገልግሎት ሰጭ መሪዎችና ባለሙያዎችን ማፍራት የሚችል አደረጃጀትና አሰራር ሊከተል ይገባል ብለዋል።
የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሸነር ዶ/ር መኩሪያ ኃይሌ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙን ውጤታማ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው የሲቪል ሰርቪስ ተቋማቱን አመራርና ባለሙያዎችን አቅም መገንባት በሚያስችለው ቁመና ላይ እንዲደርስ በርካታ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልጸው የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደርን ማዘመን የሚያስችል ሁለንተናዊ አቅም እንዲኖረው ለመድረግ ተግቶ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ንጉስ ታደሰ በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መሪዎችና ባለሙያዎችን ማብቃት በሚያስችል ቁመና እንዲደራጅ መንግስት ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
በመድረኩም በምሁራን የተጠና ጥናት ቀርቦ ውይይት የተካሄደበት ሲሆን ከተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በአመራሮች መልስና መብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
Recent News
Follow Us