News Detail
Oct 17, 2025
22 views
የትምህርት ሚኒስትሩ የ Foreign, Commonwealth & Development Office (FCDO) የኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተርን በጽ/ቤታቸው ተቀበለው አነጋገሩ።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በእንግሊዝ መንግስት የFCDO የኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተመደቡትን Amanda McLoughlin በጽ/ቤታቸው ተቀብለው በኢትዮጵያ በሚሰሩ የሪፎርም ስራዎች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
በዚሁ ወቅት የትምህርት ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ የሪፎርም ተግባራትን እየተገበረች መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም የተጀመሩ የሪፎርም ተግባራት የበለጠ እንዲሳኩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የቅድሚያ ትኩረት በሰጣቸው ጉዳዮች ላይ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።
በመሆኑም Education Transformation Operation for Learning (ETOL) ፕሮጀክት የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ እንዲፈጥን ጠይቀው፤ ለትምህርት ጥራት መውደቅ አንዱ ምክንያት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎት ማነስ በመሆኑ በዚህ ረገድ ድጋፉ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል።
አዲሷ የ FCDO የኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር Amanda McLoughlin በበኩላቸው በትምህርቱ ዘርፍ ለተጀመሩ የሪፎርም ተግባራት አድናቆት እንዳላቸው ገልጸው፣ FCDO ለኢትዮጵያ የሚያደርገው ቴክኒካል ድጋፍ ይቀጥላል ብለዋል።
በተለይም የእንግሊዝ መንግስት ድጋፍ ለማድረግ ከለያቸው አስር የአፍሪካ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም መሆኗን ጠቅሰው በ ETOL ፕሮጅክት እና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ መርሃ ግብር የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።