News Detail

National News
Oct 19, 2025 60 views

በሀረሪ ክልል በ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እውቅናና ሽልማት ተበረከተ። በሀረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ በክልሉ በ2017 የትምህርት ዘመን በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎችና ሌሎች ባለድርሻዎች እውቅናና ሽልማት አበርክቷል።

በመርሀ-ግብሩ ላይ የተገኙት ትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በሀረሪ ክልል በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የተመዘገበው 22 በመቶ ውጤት አበረታች መሆኑን ጠቁመው ክልሉ ለትምህርቱ ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት ማሳያ ነው ብለዋል።
እንደ ሀገር በትምህርት ዘርፉ የሰራና የለፋ ብቻ ውጤት የሚያገኝበት ሥርዓት እየተዘረጋ መጥቷል ያሉት ሚኒስትሩ ዛሬ የተሸለማችሁ በአቋራጭ ሳይሆን በስራና በድካም ያገኛችሁት ውጤት በመሆኑ ልትኮሩ ይገባችኋል ብለዋል።
በቀጣዩ የ2018 የትምህርት ዘመንም የ12 ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና በክልሉ ሙሉ በመሉ ከወረቀት ነፃ በሆነ መልኩ በኦላይን ለመስጠት ከክልሉ አመራር ጋር መግባባት መደረሱንም ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
በመሆኑም በክልሉ አሁን በተገኘው ውጤት መዘናጋት ሳይኖር የትምህርት ጥራትና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም ይሄ ትውልድ የሥራ ትውልድ፣ በራሱ የሚኮራ ትውልድ እንዲሆን እንደ ሀገር የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።
በዕውቅናና ሽልማት መርሀ-ግብሩ ላይ የትምህርት ሚኒስቴርና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
Recent News
Follow Us