News Detail
Apr 29, 2025
5 views
የሥርዓተ ትምህርት ሪፎርምን ከመምህራን ሙያዊ ብቃት ጋር ማስተሳሰር እንደሚገባ ተጠቆመ።
Innovation Africa 2025 ጉባዔ በአፍሪካ የሥርዓተ ትምህርት ሪፎርምን ለመተግበር የመምህራን ጥራትና ብቃትን ማረጋገጥ በሚቻልበት ዙሪያ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩ ፓናሊስት ሆነው የቀረቡት በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራን ትምህርት አመራሮች ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ሙሉቀን ንጋቱ በትምህርት ዘርፉ የመምህራንን እና የትምህርት ቤት አመራሮችን ብቃት ለማሳደግ የተለያዩ ስትራቴጂዎች ተቀርፀው ተግባራዊ እየተደረጉ እንዳሉ አንስተዋል።
በተለይም በትምህርት ዘርፉ ከተካሄዱት ሪፎርሞች ውስጥ አንዱ የሥርዓተ ትምህርት ለውጥ መሆኑን ጠቅሰው ይህንን ሥርዓተ ትምህርት ከመምህራን ስልጠና ማዕቀፍ ጋር በማጣጣም መምህራንን በተለያዩ የስልጠና ሞዳሊቲዎች እያሰለጠን እንገኛለን ብለዋል።
በዚህም በባለፈው በክረምት ከ52 ሺ በላይ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮችን በሚያስተምሩት የትምህርት ይዘትና ስነ ዘዴ ላይ ስልጠና መሰጠቱን ጠቅሰዋል።
አክለውም በቀጣይ ክረምት 84 ሺ የሚደርሱ መምህራንን በሚያስተምሩት ይዘትና ስነ ዘዴ ላይ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ስልጠና ለመሥጠት እየተሰራ መሆኑንን አንስተው በየትኛውም ሪፎርም ለመምህራን ብቃትና ጥራት ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በመድረኩም የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በሥርዓተ ትምህርት ሪፎርም የመምህራንን አቅምና ብቃት ለማሳደግ እየሰሩ ያሉትን ሥራም አጋርተዋል።