News Detail
Mar 06, 2025
118 views
የትምህርት ጥራትና ፍትሃዊነቱን ለማረጋገጥ የሚካሄዱ ስራዎች የሁሉንም የልማት አጋሮችና ባለድርሻዎች የጋራ ተሳትፎና ርብርብ እንደሚጠይቁ ተጠቆመ፤ የሂዩማን ካፒታል (Human Capital) ፕሮጀክት መክፈቻና ማስተዋወቂያ መርሃ ግብር በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በትምህርት ሚኒስትር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ መርሃ ግብሩን ሲከፍቱ እንደገለጹት የትምህርት ጥራትና ፍትሃዊነቱን ለማረጋገጥ የሁሉንም የልማት አጋሮችና ባለድርሻዎች ቅንጅት ፣ ተሳትፎና ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት ትምህርትን ለማዳረስ በተሰሩ ስራዎች የተሻለ አፈፃፀም ቢኖርም የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ አኳያ አሁንም ሰፊ ክፍተት መኖሩን ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል።፡
በትምህርት ለትውልድ መርሃ ግብር የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሳደግ፣ የመምህራንና የትምህርት አመራሮች ልማትና ሌሎችም አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን ስፋትና ጥልቀት ማሳደግ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የሁዩማን ካፒታልረ ፕሮጀክቱ በ65 ወረዳወች እንደሚተገበር የጠቆሙት ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ፕሮጀክቱን በመደገፍ ላይ ለሚገኙት የገንዘብ ሚኒስቴር አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም የዓለም ባንክና ለሌሎችም ባለድርሻዎች ምስጋና አቅርበዋል።፡
በመድረኩ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በሚካሄድባቸው ወረዳዎች የሚፈለገው ውጤት እንዲመዘገብ በትኩረትና በውጤታማነት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በዓለም ባንክ የፕሮጀክቱ ቲም ሊደር የሆኑት ሚስተር ሳመር ኤ አይ ሳመራይ በበኩላቸው የዓለም ባንክ የአጠቃላይ ትምህርት ጥራትና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ ለሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በመርሃ ግበብሩ የክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎችና ምክትል ኃላፊዎች ፣ የትምህርት ሚኒስቴር ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ፣ሴክተር መስሪያ ቤቶች የስራ ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሙዎች ፣ ከዓለም ባንክና ከ65 ወረዳዎች የተወከሉ ተሳታፊዎች ተገኘተዋል።