News Detail

National News
Mar 01, 2025 53 views

በተለያዩ ክልሎች የመምህራንና የትምህርት አመራሮችን ብቃትና ተነሳሽነት ለማሳደግ ስልጠናዎች እየተሰጡ ነው።

በሁሉም ክልሎች በተመረጡ የስልጠና ማዕከላት እተሰጠ ያለው ስልጠና በስነ-ልቦና እና ማህበራዊ ድጋፍ፣ በስራና ተግባር ተኮር ትምህርት እና በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት ማስተማር ስነ ዘዴ ላይ ያተኮረ ነው፡፡
የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) የስነልቦና እና ማህበራዊ ድጋፍ ስልጠና ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት ችግሮች በነበሩባቸው አካባቢዎች ለሚያስተምሩ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች እየተሰጠ ያለው ስልጠና መምህራን ተግዳሮቶችን ተቋቁመው የማስተማርና ስራቸውን በአግባቡ መምራት እንዲችሉ እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር ለስልጠናው ትልቅ ስራ እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ቶላ ከስልጠናው ባሻገም ሚኒስቴሩ ሞተር ብስክሌቶችን በመለገስ፣ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን መጽሃፍት ሙሉ በሙሉ አሳትሞ በማሰራጨት፣ ሞዴል ትምህርት ቤቶችን በመገንባትና በሌሎችም የትምህርትን ጥራት ለማስጠበቅ እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች እያደረገ ላለው ድጋፍ አመስግነዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንና የትምህርት አመራሮች ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሙሉቀን ንጋቱ በበኩላቸው የትምህርት ሚኒስቴር ከክልል ትምህርት ቢሮዎች ጋር በመተባበር የተለያዩ አጫጭርና የረዥም ጊዜ ስልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር ለመምህራንና ለትምህርት አመራሮች የስነልቦና እና ማህበራዊ ድጋፍ/ Psycho-Social Support/ ስልጠና የሚሰጠው ስልጠና ዓላማ መምህራንና የትምህርት አመራሮች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች የሚፈጠሩ ችግሮችን ተቋቁመው ማስተማር እንዲችሉ ለመደገፍ መሆኑን አስረድተዋል፡።
የመምህራን ትምህርት አመራር ልማትና አስተዳደር ዴስክ ኃላፊ ወ/ሮ አሰግድ ሜሬሳ በበኩላቸው ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የመምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች የመፈጸምና ማስፈጸም አቅም ለማሳደግ አጫጭር የስራ ላይ ስልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ከ6 ሺህ በላይ ለሚሆኑ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች የመፈጸምና ማስፈጸም አቅማቸውን ማሳደግ የሚያስችል አጫጭር የስራ ላይ ስልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ ወ/ሮ አሰገደች አስታውቀዋል፡፡
ስልጠናዎቹ በስራና ተግባር ትምህርት ማስተማር ስነ ዘዴ፣ በስነ-ልቦና፣ የአእምሮ ጤና እና ማህበራዊ ድጋፍ ፣ በመጀመሪያ ቋንቋ ለሚያስተምሩ መምህራን ቋንቋን የማስተማር ስነዘዴ፣ በተከታታይ ምዘና አሰጣጥ፣ በትምህርት ዕቅድ ዝግጅትና ዲጂታል ቴክኖሎጂን መጠቀም ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።
Recent News
Follow Us