News Detail

National News
Jan 05, 2025 5 views

ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ የልዩ ትምህርት ፍላጎት ያላቸው ዜጎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡና ጥራት ያለው ትምህርትና ስልጠና እንዲያገኙ ማድረግ የሁሉንም ባለድርሻዎችና አጋሮች ድጋፍና ትብብር እንደሚፈልግ ተገለጸ።

በልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርት ላይ ከአካል ጉዳተኞች ማህበራት ጋር ምክክር ተደርጓል።
የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ የምክክር መድረኩን ሲከፍቱ እንደገለጹት እድሜያቸው ለትምህርት የደረሰና ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ሁሉም ልዩ የትምህርት ፍላጎት ያላቸው ህጻናት ወጣቶችና ጎልማሶች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡና ጥራት ያለው ትምህርትና ስልጠና እንዲያገኙ ማድረግ የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ ተግባር ነው።
ልዩ የትምህርት ፍላጎት ያላቸውን ዜጎች የትምህርት ተጠቃሚነት ለማሻሻልና አካቶ ትምህርትን ለመተግበር በስራው ዙሪያ ንቁ ተሳትፎ ካላቸው የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና አጋሮች ጋር በትብብር መስራቱ ለስራው ውጤታማነት አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑንም ክብርት ወ/ሮ አየለች ተናግረዋል፡፡
በ2015 ዓ.ም በወጣው የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ልዩ ተሰጥዎና ተውህቦ ያላቸው፣ የአካል ጉዳትና ልዩ የመማር ፍላጎት ያላቸውን ተማሪዎች የሚያስተናግድ ስርአተ ትምህርት ተዘጋጅቶ ስራ ላይ እንዲውል አቅጣጫ መቀመጡንም ሚኒስትር ዴኤታዋ አመልክተዋል፡።
ልዩ ፍላጎት ያላቸው ሁሉም ህፃናት ወጣቶችና ጎልማሶች የትምህርት ጥራትና ተገቢነት ያለው ፍትሃዊ የሆነ ትምህርትና ስልጠና ተደራሽ በማድረግ በአገራቸው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ውስጥ ሙሉ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያስችል የአካቶ ትምህርት ስርዓትን ለመገንባት ስትራቴጂ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል፡፡
የትምህርት ፕሮግራሞችና ጥራትና መሻሻል መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ዩሀንስ ወጋሶ በበኩላቸው ልዩ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግና በትምህርት ቤት ውስጥ የሚያገኙትን ትምህርት ለማሻሻል በተዘጋጀው የልዩ ትምህርት ስትራቴጂ የተቀመጡ ዋና ዋና ምሶሶዎችን በመተግበር የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ በጋራ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡።
የአርብቶ አደርና የልዩ ፍላጎት ትምህርት ዴስክ ኃላፊ ወ/ሮ መሠረት በቀለ በዚሁ ወቅት ባቀረቡት ጽሁፍ ወደ ትምህርት ቤት ያልመጡና ትምህርት ቤቶችም ምቹ ባለመሆናቸው ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ በርካታ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ተማሪዎች መኖራቸውን ጠቁመው የድጋፍ መስጫ ማዕካትን በማቋቋምና የመምህራንን ክህሎት በማሳደግ የአካል ጉዳተኞችን የትምህርት ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው ማህበራት ህብረተሰቡን ማንቃትና በሚሰሩ ስራዎች ላይም የሚያስፈልጉ ምክረ ሀሳቦችን በመስጠት የአካል ጉዳተኞችን የትምህርት ተጠቃሚነት ለማሳደግ በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል።
Recent News
Follow Us