News Detail

National News
Nov 15, 2024 73 views

አገር አቀፍ አመታዊ የሳይንስ ትርኢትና ውድድር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለጸ

ትምህርት ሚኒስቴር በየአመቱ በህዳር ወር የሚከበረውን የአለም አቀፍ የሳይንስ ቀንን ምክንያት በማድረግ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ከህዳር 3-6/2017 ዓ.ም የተማሪዎችና መምህራን የፈጠራ ስራዎች አውደርዕይ እና ውድድር አካሂዷል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የሂሳብ፣ሳይንስና ሥነ-ጥበብ ዴስክ ኃላፊ አቶ ታደሰ ተሬሳ በአውደ ርዕዩና በውድድሩ ላይ የተሳተፉት በሳይንስ ትምህርቶች ለየት ያለ ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎችና መምህራን መሆናቸው ገልጸው ወደ ውድድሩ የመጡት በየክልሎቻቸውና በከተማ መስተዳድሮች ተመርጠው መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ታደሰ አያይዘውም አውደርዕዩና ውድድሩ በስምንት ዘርፎች መከናወኑንና በአጠቃላይ 124 ተማሪዎችና 20 መምህራን እንደተሳተፉ ጠቅሰው የፈጠራ ሥራዎችን ለማሳደግ የመምህራን ብቃትን ማሳደግ ወሳኝ በመሆኑ ይህንን ለማሳካት ሚኒስቴር መ/ቤቱ የአቅም ግንባታ ሥራዎች ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር በከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ የማህበረሰብ ጉድኝትና ሀገር በቀል ዕወቀት ዴስክ ኃላፊ ወ/ሮ ሰላማዊት አለሙ በበኩላቸው መድረኩ የተማሪዎችን የፈጠራ ችሎታ እና የሳይንስና ምህንድስና ሙያ ፍላጎት እንዲያድግ በማድረግ ህብረተሰቡ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ የሚያገኘው አበርክቶ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እንዲል ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ወ/ሮ ሰላማዊት መድረኩ ተማሪዎች የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች በሳይንሳዊ ዘዴ የመፍታት አቅም እንዲያዳብሩ፣እርስ በርስ እንዲማማሩ፣ የሰሯቸውን የፈጠራ ሥራዎች ይበልጥ እንዲዳብሩና የገበያ ትስስር እንዲያገኙ ከአጋርና ባለድርሻ አካላት ጋር እንዲተዋወቁ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል።
በማጠናቀቂያው በሰምንቱም ዘርፎች ከ1ኛ እስከ 3ኛ ለወጡ ተወዳዳሪዎች የማበረታቻ ሽልማቶች ተሰተዋል፡፡
መድረኩንም በትብብር ያዘጋጁት ትምህርት ሚኒስቴር፣አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣አገር አቀፍ ስቴም ፓወር፣ አገር አቀፍ ስቴም ሲነርጂ፣ጃይካ እና ትምህርት ለኢትዮጵያ የተሰኙ ተቋማትና ድርጅቶች እንደሆኑ በመድረኩ ተገልጿል፡፡
ይህ አገር አቀፍ አመታዊ የሳይንስ ትርኢትና ውድድር በዛሬው እለት የሚጠናቀቅ ይሆናል።
Recent News
Follow Us