News Detail
Aug 03, 2024
1.2K views
የከፍተኛ ትምህርት፣ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ የምርምር ተቋማትና የኢንዱስትሪ ትስስር አዋጅን ለማስጀመርና የማስፈጸሚያ የህግ ማዕቀፎችን ለማጽደቅ የሚያግዝ መርሃ-ግብር ተካሄዷል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ የትስስር ምክር ቤቱ አመራር አካላት፣የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሜቴ ሰብሳቢዎች፣የሴክተር መሥሪያ ቤቶችና ቢሮዎች አመራሮችና አግባብነት ያላቸው ባልሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትርና የትስስር ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ክቡር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የትምህርት ተቋማት በተለይ የትስስር አዋጁን በሚፈለገው ፍጥነትና አግባብ በመተግበር ዘርፉን ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡
በኢንዱስትሪዎች የሚደረጉ ልምምዶች ሰልጣኞች ተጨባጭ እውቀትና ክህሎቶችን ይዘው እንዲወጡ ከማድረግ ባሻገር ብቁ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እንደሚያደርጋቸውም ገልጸዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትርና የትስስር ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ ክቡር አቶ መላኩ አለበል መርሃ-ግብሩን በከፈቱበት ወቅት እንዳተናገሩት፤ የምርምርና የትምህርት ተቋማት በትስስሩ የተፈጠረውን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ከኢንዱስትሪ ጋር ያላቸውን ቁርኝት በማጠናከር የዘርፉ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ሊሰሩ እንድሚገባ ገልጸዋል።
ትስስሩ በተለይ ተማሪዎች በንድፈ ሐሳብ የሚያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ኢንዱስትሪውን ለመደገፍና በጋራ ለመሥራት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም አንስተዋል።
ትምህርት፣ ስልጠናና ምርምርን ማበረታታት ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት የሚያስችል ሲሆን ለስኬታማነቱ የከፍተኛ ትምህርት፣የሥልጠናና የምርምር ተቋማትን ከኢንዱስትሪዎች ጋር ማስተሳሰር አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ኮራ ጡሹኔ በበኩላቸው፤ የትስስር አዋጁ ተበታትኖ የቆየውን የትምህርት ተቋማትና የኢንዲስትሪ ግንኙት የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር ተማሪዎች በኢንዱስትሪ ውስጥ የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ ከማድረግ አንፃር ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራር እንዳልነበር ጠቅሰው ይህ ክፍተት በትስስር አዋጁና አዋጁን መሰረት በማድረግ በተዘጋጁና በቀጣይ በሚጸድቁ የህግ ማዕቀፎች የነበረውን ክፍተት የሚሞላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመርሃ-ግብሩ ላይ ለትስስር አዋጁና ሌሎች ተያያዥ የህግ-ማዕቀፎች እዚህ ደርጃ መድረስ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ አመራሮችና ባለሙያዎች የእውቅናና ማበረታቻ ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል።
Recent News
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምግብ ሜኑ ተመሳሳይ እንዲሆን ተወሰነ።
Dec 09, 2024
የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎትን ለማሳደግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ።
Dec 07, 2024