News Detail

National News
Jan 26, 2023 3.9K views

በሲዳማ ክልል በአንድ ባለሀብት በ7 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባ ትምህርት ቤት ተመረቀ

ጥር 18/2015 ዓም (ትምህርት ሚኒስቴር) የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ያደረገውን ጥሪ ተከትሎ በአንድ ባለሀብት በ7 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትናንት ተመረቋል።
በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ተገኝተው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ የክልሉ መንግስት ጥራት ያለው ትምህርት በማዳረስ ትውልዱ እንዲታነፅ እየሰራ ይገኛል ያሉ ሲሆን የዛሬውም አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
በዘንድሮ ዓመት ከመቶ ያላነሰ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ሰርቶ ለማጠቃለል እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል። ይህ ራዕይ ትውልድን የሚገነባ መሆኑን ገልፀው ባለሃብቶችም በዚህ መልካም ስራ እንዲሳተፉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ም/ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ በየነ በራሳ በበኩላቸው ይህ ትምህርት ቤት የመንግስትና ህዝብ መተባበር ማሳያ ነው ብለዋል።
መንግስት የትምህርት ተሃድሶ አብዮትን ሰንቆ እየሰራ ነው ያሉ ሲሆን በዚህም የመምህራን ክህሎት የማሳደግ ስራ እና የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን የመገንባት ስራ በትኩረት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ትምህርት ቤቱን ገንብተው ያስረከቡት ባለሀብት አቶ ዱካለ ዋቀዮ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት የትምህርት ተሃድሶ ራዕይ ሰንቆ እኛ በክልላችን በራሳችን አቅም ድጋፍ እንድናደርግ ጥሪ ስላደረገልን እናመሰግናለን፤ መንግስትና ህዝብ ከተባበረ ከዚህም የተሻለ መስራት ይቻላል ብለዋል።
ምንጭ ፡ የሲዳማ ብሔራዊ ክልል ትምህርት ቢሮና ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት
Recent News
Follow Us