News Detail
Nov 21, 2022
3.5K views
"የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ ይገኛል "ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ የትምህርት ሚኒስትር
ህዳር 9/2015ዓም. (ትምህርት ሚኒስቴር) 31ኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባዔ በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በጉባኤው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ(ፕ/ር) በትምህርት ዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ በተወሰደው ሪፎርም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሰሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
በትምህርት ዘርፉ የመምህራንና የትምህርት አመራሮች ብቃት ማነስ ፣ የሞራል ስብራት፣ የፓለቲካ ጣልቃ ገብነት እንዲሁም የአካባቢዊ የፓለቲካ ስሜት መተሳሰር ከፍተኛ ችግሮች መሆናቸውን በመለየት በርካታ የሪፎርም ስራዎች መጀመራቸውን ጠቁመዋል ።
ሚኒስትሩ አያይዘውም ሀገራችን አሁን ወደ ዘላቂ ሰላም የምታደርገው ጉዞ በብዙ ወገኖች መስዋዕትነት የተገኘ በመሆኑ ሁሉም አካል ሊንከባከበው እንደሚገባ አሳስበዋል ።
ሀገራችን የነበረውን ችግር በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት የምታደርገው ጥረት በትምህርት ዘርፉ የተጀመሩ ሪፎርሞችን በትልቅ ትልም ለማየት የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል ።
ትምህርት የአንድ አካል ስራ ባለመሆኑ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ሚኒስትሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በእንኳን መልዕክታቸው በዘርፉ የተካሄዱ ሪፎርሞች እስካሁን ያሉበትን ደረጃ በመፈተሽ ተገቢ አቅጣጫ በማስቀመጥ ውሳኔ የሚወሰንበት ጉባዔ እንዲሆን ተመኝተዋል።
በጉባኤ የሚተላለፉ ውሳኔዎችምን ተግባራዊ ለማድረግ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል ።
በጉባኤው በ2014 ዓ.ም አንኳር ስኬቶች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንዲሁም በ2015 ዓ.ም የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቷቸው የሚሰሩ ቁልፍ ተግባራት ላይ በመወያየት አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።