News Detail
Nov 21, 2022
3K views
በቀጣይ አመታት የመንግስት ትኩረት ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ያሉ ትምህርት ቤቶችን ማስፋት ነው"-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ህዳር 6/2015 ዓም. (ትምህርት ሚኒስቴር) በቀጣይ አመታት የመንግስት ትኩረት ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ያሉ ትምህርት ቤቶችን ማስፋት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ገለጹ።
ላለፉት 4 ዓመታት አንድም ዩኒቨርስቲ እንዳልተከፈተ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥም መንግስት አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች የመክፈት ዕቅድ እንደሌለው ገልጸዋል፡፡
በሚቀጥሉት ዓመታት የመንግስት ትኩረት በቅድመ መደበኛ (መዋዕለ ህጻናት) ፣የመጀመሪያ ደረጃ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤቶች ላይ አስተማማኝ መሰረት መጣል እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዩኒቨርስቲዎች በሚጠበቅባቸው ደረጃ ማደግ እና ራሳቸውን ወደ ማስተዳደር መሸጋገር እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ይህንን የጀመሩ ስለመኖራቸውም አንስተዋል፡፡
ጥራት ያለው ትምህርት በዩኒቨርስቲዎች መጀመር እንዳለበት የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ከዩኒቨርስቲዎች ተመርቀው የሚወጡ ዜጎችም ችግር ፈቺ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
በትምህርቱ ዘርፍ የተጠቀሱት መሰረታዊ ጉዳዮች ሲሟሉ ትክክለኛ የዩኒቨርስቲ ጥያቄ ያለባቸው አካባቢዎች ወደፊት ምላሽ እንደሚያገኙ ጠቁመዋል፡፡