News Detail

National News
Sep 19, 2022 2.6K views

ያጋጠመንን የትምህርት ጥራት ችግር ለማሻሻልና ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ለመስጠት አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ተገለጸ፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ትግበራ ፣ በ2015 ዓ.ም ትምህርት አጀማመር እና በተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

በያዝነው 2015 ዓ.ም  ተግባራዊ የሚደረገው አዲሱ ስርአተ ትምህርት ተገቢውን ዕውቀትና  ክህሎት ከስነ ምግባር ትምህርት ጋር አጣምሮ ለመስጠት የሚያስችል በመሆኑ  በትምህርት ዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን  ለመሙላት ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው በትምህርት ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ሠርዓተ ትምህርት ዴስክ ሃላፊ ወ/ሮ ዛፉ አብርሃ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አብራርተዋል፡፡

ዛሬ መስከርም 6 ቀን 2015 ዓ.ም የትምህርት ሚኒስቴር ባዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡት ወ/ሮ ዛፉ  ከዚህ በፊት የነበረው ስርዓተ ትምህርት የነበሩበት ክፍተቶች  በጥናት የተለየ  መሆኑንም አክለው ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ሀገር በቀል እውቀትን ፣ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ፣ እንዲሁም  ተግባር ተኮር ትምህርትን ከስነ ምግባር ትምህርት ጋር አቀናጅቶ ለመስጠት እንዲያስችል ተደርጎ የተቀረጸ በመሆኑ በእውቀትና ከህሎት የታነጸ ትውልድ ከመገንባት አንጻር ፋይዳው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል ፡፡

በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት የአደረጃጀት ለውጥ የተደረገ  ሲሆን በዚህም 6፣2፣2፣2 የነበረው አደረጃጀት ቅድመ መደበኛ  2ዓመት  አንደኛ ደረጃ  ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል  6  ዓመት መካከለኛ ደረጃ  7 እና 8ኛ ክፍል 2 ዓመት እንዲሁም 2ኛ ደረጃ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል 4 ዓመት(2 ፣6 ፣2፣4) እንዲሆን ተደርጓል ፡፡

በ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከቅድመ መደበኛ እስከ 8ኛ ከፍል አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን በ9ኛ እና 10ኛ ክፍል ደግሞ የሙከራ ትግበራ በተመረጡ 80 ትምህርት ቤቶች የሚካሄድ መሆኑን ወ/ሮ ዛፉ ገልፀዋል፡፡

በሌላ በኩል የትምህርት  ፕሮግራሞች ጥራትና ማሻሻል መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ዩሀንስ ወጋሶ በአገሪቱ ሁሉም ክልሎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች መስከረም 9 /2015 ዓም  ተከፍተው የመማር ማስተማር ስራ  እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል፡፡

በልዩ ልዩ አስገዳጅ ምክንያቶች ሰኞ  መስከረም 9 /2015 ዓም ትምህርት የማይጀምሩ ትምህርት ቤቶች ቢኖሩ ተገቢውን  ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የመማር ማስተማር ስራ እንዲጀምሩ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አመለወርቅ  ህዝቅኤል  በበኩላቸው ሁሉም እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ህብረተሰቡ  የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Recent News
Follow Us