News Detail

National News
Sep 07, 2025 33 views

ጳጉሜ 2 የህብር ቀን “ብዝሃነት የኢትዮጵያ ጌጥ” በሚል መሪ ቃል ተከበረ፤ የትምህርት ፣ የሠላም፣ የፍትህ እና የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር መ/ ቤቶች የህብር ቀንን '' ብዝሃነት የኢትዮጵያ ጌጥ '' በሚል መሪ ቃል በጋራ አክብረዋል።

የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ ቀኑ በፓናል ውይይቱ በተከበረበት ወቅት እንደገለጹት ብዝሃነት የሀገራዊ ስኬቶቻችን መሠረት በመሆኑ የወል ትርክት ግንባታን ማጠናከር ከሁላችንም እንደሚጠበቅ ጠቁመው የብዝሃ ኢትዮጵያ ጌጦችን ማጽናትና በቀጣይም አዳዲስ ድሎችን በማስመዝገብ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ከዚህ ጋር አያይዘው ለጋራ ራዕያችን እውን መሆን ብዝሃነትን በማስተናገድ የተገነባ ጠንካራ አገራዊ አንድነት፣ መተሳሰብ፣ መቻቻል፣ ፍቅርን በይቅርታ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ክብርት ወ/ሮ አየለች አክለውም ትምህርት ቤቶች የብዝሃ ኢትዮጵያ መገለጫ በመሆናቸው በትምህርትና ስልጠና ፖሊሲው ብዝሃነትን የሚቀበሉ፣ የሚከባበሩ፣ የሚተሳሰቡ ፣አብሮ ለመኖር ፈቃደኛ የሆኑ ዜጎችን በመፍጠር የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ከታችኛው እርከን ጀምሮ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ መሃመድ እድሪስ በበኩላቸው ቀኑን ስናከብር ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጠናከር፣ የብዝሃነት ትሩፋታችንን በማስቀጠልና ከወል ትርክታችን በመነሳት የጋራ ነጋችንን በማበጀትና የተጀመሩ የሰላም ጥረቶቻችንን በማስቀጠልና በማጽናት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የፓናል ውይይቱ ዓላማም ስኬቶችን፣ መነሳሳቶችን፣ ብሄራዊ ጥቅሞችንና ፍላጎቶችን በማስገንዘብ ፣ ስኬቶቻችንን ለማስቀጠልና ተግዳሮቶችን ለመሻገር የዛሬን ነባራዊ ሁኔታና የነገ ስኬታችን ምስጢር ህብራችን መሆኑን ለማስገንዘብ ነው ብለዋል።
የፍትህ ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሃና አርአያ ስላሴ በበኩላቸው ህብረ ብሄራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት በተሻለ መደላድል ላይ እንደምንገኝ ጠቁመው ኢትዮጵያዊነት በአሰባሳቢ የወል ትርክት ከፍ እንዲል እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ከወል ትርክ ባሻገር መንግስት ማሻሻያዎች በማድረግ አሳታፊና አካታች የፖለቲካ አውድ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑንና ህብረብሄራዊ ኢትዮጵያን ለመገንባት ከህጻናት ጀምሮ መሰረቱ የተስተካከለ ትውልድ መፍጠር የሁላችንም የጋራ ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል።
በእለቱ “የጋራ ታሪክና ባህል ለብዝሃ ማንነት” በሚል ርዕስ በፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ፣ “ማህበራዊና ባህላዊ እሴቶቻችን” በሚል ርዕስ በዶክተር ተካልኝ አያሌው፣ “የሚዲያ ሚና ለህብረ-ብሄራዊ አንድነት ግንባታ” በሚል ርእስ ደግሞ በዶክተር ተስፋዬ በዛብህ የውይይት መነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ብዝሃነት የኢትዮጵያ ጌጥ በሚል መሪ ቃል በተከበረው በዚሁ የህብር ቀን በዓል ላይ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ምሁራን፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ ወጣቶችና ሌሎችም ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
Recent News
Follow Us