News Detail
Oct 10, 2025
27 views
ትምህርት ሚኒስቴር በከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ለ2018 ዓ.ም ሊተገበሩ በታቀዱ ቁልፍ የውጤት አመላካቾች ዙሪያ ከመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የአፈጻጸም ውል ስምምነት ተፈራረመ ፤
ትምህርት ሚኒስቴር በከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ለ2018 ዓ.ም ሊተገበሩ በታቀዱ ቁልፍ የውጤት አመላካቾች ከመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የአፈጻጸም ውል ስምምነት (Performance contract) የዩኒቨርሲቲዎቹ የቦርድ አመራሮች በተገኙበት አካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ዩኒቨርሲቲዎች ቁልፍ የውጤት አመላካቾችን መሠረት በማድረግ ቆጥረው የወሰዱትን ተግባራት አፈጻጸም ጥራትና ተዓማኒት ባለው መረጃ አስደግፈው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
በተለይም በዩኒቨርሲቲዎች እየተተገበረ ያለው የመስክ ልየታ ፕሮግራም የአካባቢያቸውን ጸጋ እና በሂደት ያካበቱትን እምቅ አቅም አስተውለው በመለየት የየራሳቸው ተፈላጊነትና ተወዳዳሪነት እንዲኖሯቸው የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው ተቋማቱ በተማሪዎች ዘንድ ተመራጭ ለመሆኑ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በቀጣይም በአጭር ጊዜ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በሀገሪቷ የትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ሥርዓት የሚመዘኑ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ ስለመምህራን፣ ተማሪዎች፣ ምሩቃን ያሉበትን ደረጃና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎችን በትክክል ማቅረብ ከዩኒቨርስቲዎች እንደሚጠበቅ ገልጸው ይህንን ማድርግ የማይችል የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ተጠያቂ እንደሚሆን አሳስበዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሹኔ በበኩላቸው ዛሬ የቦርድ አመራሮች በተገኙበት የተፈረመው ውል ሀላፊነትና ተጠያቂነትን በማስፈን የትምህርት፣ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ጥራትና ተገቢነትን ለማስጠበቅ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህ የሥራ አፈጻጸም ስምምነት ውል የመፈራረሙ ዓላማ ጥሩ ውጤት የሚያስመዘግቡ ሥራ አስፋጻሚዎች የበለጠ የሚበረታቱበት፣ ዝቅተኛ አፈጻጸም የሚያስመዘግቡ ደግሞ ተጠያቂ የሚሆኑበት ሥርዓትን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሆነም ሚኒስትር ዴኤታው አንስተዋል።
አክለውም የአፈጻጸም ስምምነቱ ውል የክትትልና ግምገማ ሥርዓት ያለው መሆኑን ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲዎች የተፈራረሙበትን ቁልፍ የውጤት አመላካቾችን መሰረት በማድረግ በተልዕኳቸው ላይ አትኩረው እንዲሰሩ አስገንዝበዋል፡፡