News Detail
Oct 14, 2025
22 views
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲሰጥ የነበረው የ2018 የድህረ ምረቃ ትምህርት መግቢያ ፈተና ተጠናቋል፤ ፈተናው ለመውሰድ ከተመዘገቡ 29 ሺ491 አመልካቾች መካከል 96 በመቶ ፈተናውን ወስደዋል፡፡
የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ ኤባ ሚጀና (ዶ/ር) እንደገለጹት የ2018 የድህረ ምረቃ ትምህርት መግቢያ ፈተና በተያዘለት ጊዜና አግባብ ተጠናቋል፡፡
በ2017 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ይሰጥ የነበረው የድህረ ምረቃ መግቢያ ፈተና በተለያዩ ምክንያቶች ተራዝሞ ጥቅምት 3 ቀን 2018 ዓ.ም. በ53 የፈተና ማዕከላት መሰጠቱንም ዶክተር ኤባ ገልጸዋል፡፡
ፈተናውን በመንግስትና በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመዝግበው ለመማር ፍላጎት ያላቸው 29ሺህ 491 አመልካቾች ተመዝግበው 96 በመቶ ያህሉ ፈተናውን መውሰዳቸውን መሪ ስራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል፡፡
በሁሉም ፈተና ማዕከላት በቂ ሱፐርቫይዘሮች፣ ፈታኞችና የአይሲቲ ባለሙያዎች በመመደባቸውና የኢንተርኔትና የመብራት መቆራረጥ እንዳይኖር ተገቢው ዝግጅት በመደረጉ የዘንድሮውን ፈተና ከወትሮው በተሻለ ዲሲፕሊን መምራት መቻሉንም ዶክተር ኤባ ገልጸው የፈተናው ውጤትም በቅርቡ ለተማሪዎች ይፋ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
የድህረ ምረቃ ትምህርት መግቢያ ፈተና (NGAT) ከሌሎች አገር አቀፍ ፈተናዎች የተለየና የ2ኛ እና የ3ኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን መቀጠል የሚፈልጉ አመልካቾች ለትምህርቱ ምን ያክል ዝግጁ ናቸው የሚለውን ለማረጋገጥ ደረጃውን ጠብቆ የሚሰጥ ምዘና መሆኑም ጨምረው አብራርተዋል፡፡