News Detail
Apr 11, 2025
20 views
የ “ትምህርት ለትውልድ” ንቅናቄ የኢትዮጵያ ወላጆች ለልጆቻቸው ትምህርት ምን ያህል እንደሚተጉ ያየንበት ነው። ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ የ9 ወራት እቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ ተካሂዷል።
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የአንድ ሀገር የትምህርት ሥርዓት ከተበላሸ ሀገር መሆን አይችልም፤ ለዚህም እንደ ሀገር የትምህርት ሥርዓቱን ከመሠረቱ ለማስተካከል በርካታ የሪፎርም ተግባራት ተቀርፀው ተግባራዊ እየተደረጉ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
በተለይም የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት በሟሟላት ምቹ የመማሪያ ከባቢን ለልጆች ለመፍጠር በተጀመረው የ”ትምህርት ለትውልድ” ንቅናቄ እስካሁን ከ52 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ሀብት በማሰባሰብ፤
ከ30 ሺ በላይ ቅድመ አንደኛ ደረጃ፣ ከ8 ሺህ በላይ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ከ22 ሺ በላይ ነባር ትምህርት ቤቶች ጥገናና እድሳት ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
ይህም የኢትዮጵያ ወላጆች ለልጆቻቸው ትምህርት ምን ያህል እንደሚተጉ ያየንበት ነበር ብለዋል።
አያይዘውም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የመምህራን ሚና የላቀ መሆኑን በማንሳት መምህራንን ተጠቃሚ የሚያደረግ የመምህራን ባንክ ለማቋቋም እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው የትምህርት ሥራ በጋራ ተባብረን ከሰራንና የራሳችንን አቅም አሟጠን ከተጠቀምን በርግጥም በትምህርቱ ዘርፍ ውጤት ማምጣት ይቻላል ብለዋል።
ከምንም በላይ መምህራን ለሙያቸው ታማኝ ሆነው ከሰሩና በጋራ ከተንቀሳቀስን በትምህርት ሥርዓቱ ለውጥ አምጥተን የገጠሙንን የትምህርት ሥብራቶች መጠገን እንችላለን ያሉት ርዕሱ መስተዳድሩ ፤
በዚህ መድረክ እንደ ክልል ባለፉት 9 ወራት በትምህርት ዘርፉ የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገም በቀሪ ጊዜያት የቀሩትን ለመፈፀም ተስማምተናልም ብለዋል።
በመድረኩም ባለፉት 9 ወራት የተሻለ አፈፃፀም ያስመዘገቡ መምህራን፣ ርዕሳነ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮች ፣ዞኖችና ወረዳዎች እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።