News Detail

National News
Aug 29, 2024 880 views

ለትምህርት ፍትሃዊነትና ጥራት መረጋገጥ የመምህራንና የትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑ ተጠቆመ።

የ33ኛው አገር አቀፍ የትምህርት ጉባዔ የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
መድረኩን የከፈቱት የተከበሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት ስምሪትና የቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ለትምህርት ፍትሃዊነትና ጥራት መረጋገጥ የመምህራንና የትምህርት አመራሮች ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የትምህርት ፍትሃዊነት እንዲረጋገጥና ጥራቱም እንዲጠበቅ ሁላችንም ርብርብ ማድረግ እንዳለብን ተናግረዋል። የመምህራራንና የትምህርት አመራሮች የብቃት ደረጃ በሚፈለገው ደረጃ ማድረስና ሙያዊ ስነምግባርን ማሳደግ እንደሚገባም ዶክተር ነገሪ ጠቁመዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ በበኩላቸው ትምህርት ብቁና በቂ የሰው ኃይል በማፍራት የሀገርን እድገት በማፋጠን ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው አስገንዝበዋል።
በ2016 የትምህርት ዘመን በትምህርት ቤት ምገባ መርሀግብር ከመንግስት፣ ከህብረተሰቡ እና ከአጋር ድርጅቶች 14.7 ቢሊዮን ብር ማሰባሰብ መቻሉን ተናግረዋል።
በትምህርት ለትውልድ መርሃ ግብ በአንድ አመት ውስጥ 27.4 ቢሊዮን ብር በማሰባሰብ ትምህርት ቤቶች እንዲገነቡ፣ እንዲጠገኑና ግብአቶችም እንዲሟሉ መደረጉን ወ/ሮ አየለች አስረድተዋል፡፡
በትምህርት ዘመኑ ከቅድመ አንደኛ ደረጃ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ምዝገባ፣ መጻሕፍት ስርጭት፣ በመምህራንና የየትምህርት ቤት አመራሮችን ብቃት ማሳደግና በሌሎችም ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን አመልክተዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በሚቀርቡ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት በመስጠት በመወያየት የነቃ ተሳትትፎ በማድረግ የድርሻቸውን እንዲወጡም ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በበኩላቸው የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ በአንድ ሰው ወይም በአንድ ተቋም ብቻ የሚተገበር ተግባር ባለመሆኑ የቡድን ስራ ሁለንተናዊ ትብብር እና የተቀናጀ ትግበራን እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።
Recent News
Follow Us