News Detail

National News
Feb 02, 2024 746 views

በክልሉ የትምህርት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ያለውን ሀብት በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል-ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ እና ካቢኔ አካላት ጋር በክልሉ የትምህርት ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ዉይይት አድርገዋል ።
 
በውይይት መድረኩ በክልሉ በቀጣይ የትምህርት ስርዓቱን ማሻሻል እና ማጠናከር በሚቻልበት መንገድ ላይ በሰፊው ምክክር ተደርጓል።
 
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የክልሉ የትምህርት ስርዓቱን ውጤታማ ለማድረግ በክልሉ የትምህርት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ያለውን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ከትምህርት ስርዓት ጋር አስተሳስሮ መምራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
 
በየጊዜው የትምህርት ስራ ያለበትን ሁኔታ እየገመገሙ ቀጣይ አቅጣጫ እያስቀመጡ መሄድ ተገቢ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
የትምህርት ስራ ተማሪዎችን ማስተማር ብቻ ሳይሆን ለተማሪዎች በቂ እውቀትና ክህሎት ማሳደግ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚጠይቅ ገልፀው ለዚህም ትምህርትን ከፖለቲካ ነፃ አድርጎ መምራት ይጠይቃልም ብለዋል፡፡
በክልሉ የትምህርት ዘርፉን ለመደገፍ የትምህርት ሚንስቴር 3 መኪና እና 48 ሞተር ሳይክሎችን ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡
በ"ትምህርት ለትውልድ" ንቅናቄ የትምህርት ቤቶችን ደረጀ ከመሻሻል አኳያ በክልሉ የተሰራው ስራ የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው ህብረተሰቡን በማስተባበር ይህንን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አንስተዋል፡፡
 
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ክልሉ ከተቋቋመ ወዲህ በክልሉ የትምህርት ስርዓት ለማሻሻል እና ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አብራርቷል።
 
ይህንን ለማስጠበቅ የክልሉ መንግስት በመምህራን ልማት፣ መሠረተ ልማት፣ የመመሪያው ቁሳቁስ የማሟላት እና በአርብቶ አደር አካባቢ የተማሪዎች ምገባ ስርዓትን ተግባራዊ በማድረግ ሰፊ ስራ እየሰራ እንዳለ ገልፀዋል ።
 
በአሁኑ ሰዓት ዝቅተኛ የተማሪ ውጤት የተመዘገበውን በመቀየር የተሻለ የትምህርት ስርዓት ለመገንባት የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በማጠናከር ላይ በቀጣይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራም አመልክቷል።
 
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ በክልሉ ያሉ 90% የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ከሚፈለገው ደረጀ በታች መሆናቸውን ጠቅሰው ይህንን ለመቅረፍ የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄን እውን በማድረግ ትምህርት ቤቶችን ደረጀ ለማሻሻል ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
 
ለዚህም ከ261 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ መሰብሰቡንና የትምህርት ስራን ውጤታማ ለማድረግ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ምርጥ ተሞክሮዎችን ወደ ክልሉ በማምጣት የትምህርት ዘርፉን ለመቀየር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
 
በውይይቱ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል ሲል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ዘግቧል ።
Recent News
Follow Us