News Detail
Mar 10, 2022
1.2K views
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በኢትዮጵያ ከፊላንድ አምባሳደር ሆሎፔነን ኦቲ ጋር ተወያዩ።
ሚኒስትሩ የፊንላንድ መንግስት በትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ፕሮግራም እና በልዩ ፍላጎት አካታች ትምህርት ላይ እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና እውን አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት በሚፈለገው ደረጃ ላይ ባለመድረሱ ጠንካራ ስራ መስራት እንደሚጠይቅ የጠቀሱት ሚኒስትሩ በጦርነት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን በተሻለ እና ደረጃውን በጠበቀ ዲዛይን ለመገንባት እንደታቀደና በዲዛይኑ ፅንሰ ሃሳብ ዙሪያም ገለፃ አድርገዋል።
በኢትዮጵያ የፊንላድ አምባሳደር ሆሎፔነን ኦቲ በበኩላቸው አገራቸው የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም በመዘርጋቷ የትምህርት ጥራት እንዲኖርና የትምህርት ስርዓቱ ውጤታማ እንዲሆን ትልቅ እገዛ እንዳደረገ ገልፀዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል በሚደረጉ የሁለትዮሽ ትብብር ስራዎች በዋናነት የትምህርት ፍትሃዊነት እና አካታችነት ትኩረት የሚሰጥባቸው ተግባራት ሲሆኑ የመምህራን ስልጠናን እንደሚያካትትም አብራርተዋል።
የትምህርት ቤቶች ምገባን ለማጠናከርና ለአደጋ ጊዜ ትምህርት ፕሮግራም የሚውል 3 ሚሊዮን ዩሮ እርዳታ መሰጠቱን ገልጸዋል።
በቀጣይ በቅርብ በሚዘጋጀው የሁለትዮሽ ትብብር ስምምነት ሰነድ ላይ የትምህርት ዘርፉ የጥራት ሪፎርም ስራዎች ትኩረት ይሰጣቸዋል ተብሏል።