News Detail
Sep 19, 2025
36 views
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተማሪዎችን የማንበብ ክህሎትና ፍላጎትን ማሳደግ እንደሚገባ ተጠቆመ። አለም አቀፍ የንባብ ቀን "በቴክኖሎጂ ዘመን ንባብን ማዳበር" በሚል መሪ ቃል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጂንካ ከተማ ተከብሯል።
በመድረኩ ላይ የትምህርት ጥራትን አስጠብቆ ለመሄድ የተማሪዎችን የንባብ ክህሎትን በየጊዜ ማሳደግ እና በትምህርት ቤቶች ውስጥ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ይጠበቃል፤ ለዚህም ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተጠቁሟል።
ትምህርትን በፍትሃዊነት ለሁሉም ዜጎች በጥራት ለማድረስ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ተቀርፆ እየተተገበረ ሲሆን በተለይም አዲስ የአጠቃላይ ትምህርት አዋጅ ፀድቆ ወደ ተግባር ገብቷል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የነገው ትውልድ እጣፈንታ የሚወሰነው ዛሬ መሠረቱ ላይ በሚሰራው ሥራ በመሆኑ የልጆችን የንባብ ክህሎት ማሳደግ እንደሚገባም ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ የልጆች የማንበብ ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቶ አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል የተባለ ሲሆን ይህንን ችግር ለመቅረፍ በትኩረት መሥራት ይጠበቃል።
በተለይም ቴክኖሎጂ የዚህ ዘመን ስጦታ ቢሆንም አጠቃቀሙን መግራትና እኛ በምንፈልገው መልኩ በመጠቀም የንባብ ባህላችን መመለስ የሁላችን ጉዳይ ሊሆን ይገባል ተብሏል።
በመድረኩም የኢትዮጵያ ቤተመፅሃፍትና ቤተ መዛግብት አገልግሎት እና ኢትዮጵያ ታንብብ የተባለ ድርጅት የተማሪዎችን የንባብ ባህል ሊያዳብሩ የሚችሉ የተለያዩ መጽሐፍትን ለትምህርት ቤቶች ድጋፍ አድርገዋል።
ይህ ባለፈው ሳምንት በአለም ለ58 ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ46ኛ ጊዜ የተከበረው የአለም የንባብ ቀን ከወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ጋር በትብብር የተዘጋጀ መሆኑም ተገልጿል።