News Detail
Sep 19, 2025
46 views
እየተቀየረ ያለውን የአለም ሁኔታ ሊሸከሙ የሚችሉ በሁሉም ዘርፍ እውቀትና ክህሎት ያላቸው ተወዳዳሪ ልጆችን ማፍራት እንደሚገባ ተጠቆመ። ትምህርት ሚኒስቴር በሀረሪ ክልል የሚያስገነባው ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ የሚኒስቴሩና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተጀምሯል።
በዚሁ ወቅት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በትምህርት ሥርዓቱ መጪውን ዓለም መሸከም የሚችሉ እውቀትና ክህሎት ያላቸው በራሳቸው የሚተማመኑ ተወዳዳሪ የሆኑ ልጆችን ማፍራት ይገባል፤ ለዚህም የተጀመረው ሪፎርም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በተለይም በትምህርት ያለው ኢፍትሃዊነትን በማስቀረት ዜጎች እኩል ትምህርት በማገኘት እኩል ተወዳድረው የሚማሩበትን ሥርዓት መፍጠር አለብን ብለዋል።
ለዚህም 50 ሞዴል እንዲሁም 13 ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለመገንባት ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
ይህም ሁሉም ዜጎች እኩል ተወዳድረው ውጤት የሚያገኙበትን ሥርዓት ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን የጠቀሱት ክቡር ሚኒስትሩ ይህ ዛሬ ግንባታው የተጀመረው ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው ክልሉ በ2017 የትምህርት ዘመን ለትምህርት ዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
በቀጣይም ለትምህርት ጥራትና ፍትሃዊነት መረጋገጥ የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ያሉ ሲሆን ዛሬ ግንባታው የተጀመረው ሞዴል ትምህርት ቤትም ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑን ጠቅሰዋል።
ትምህርት ሚኒስቴር ለትምህርት ቤቱ ግንባታ ድጋፍ ስላደረገ አመስግነው ግንባታው እስኪጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ገልፀዋል።
በመድረኩም የትምህርት ቤቱ ግንባታ በአንድ ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የተገለፀ ሲሆን በተባለለት ጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ በትምህርት ሚኒስቴርና በክልሉ ትምህርት ቢሮ መካከል ሥምነት ተፈርሟል።
ስምምነቱን የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፉ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ዎዬሳ ፈርመውታል።