News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Sep 21, 2020 630 views

በትምህርት ቤቶች አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ትምህርት ለመጀመር ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ ነው:-ትምህርት ሚኒስቴር

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለ 7 ወራት የተቋረጠውን መደበኛ ትምህርት ለማስቀጠል ትምህርት ሚኒስቴር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ፡፡

መንግስት በትምህርት ቤቶች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል፣ የውሃ እና የእጅ ማፅጃ አቅርቦቶችን በማሟላት እንዲሁም ትምህርት ቤቶችን የማፅዳት ስራዎችን በማከናወን መደበኛ ትምህርት እንደሚጀመር ተገልጿል፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ.) ትምህርት ቤቶች ሲከፈቱ ተማሪዎች እንደየ ደረጃው ወደ ክፍል ገብተው ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ የገለፁ ሲሆን ትምህርት ሲጀመርም በአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የሚጀመር መሆኑን እና በቀጣይም ሌሎች የትምህርት ክፍሎች ወደ መደበኛ ትምህርቱ እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡

በትምህርት ቤቶች የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተቀመጡ ጥንቃቄዎች ሙሉ በሙሉ የሚተገበሩ መሆኑን እና የትምህርት አሰጣጡ ሂደትም በፈረቃ የሚሰጥ መሆኑንም ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡

የፈረቃ ስርዕቱም እንደየአካባቢው ሁኔታ ከ 2 እስከ 3 ሊሆን እንደሚችልም ተገልጿል፡፡

የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በትምህርት ቤት ውስጥ መምህራኖች ትልቁን ሃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ የተገለፀ ሲሆን ወላጆችም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ሲልኩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።

መደበኛ ትምህረቱም መንግስት ውሳኔ እንዳሳለፈ እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስፈላጊውን የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመተግበር ትምህርት ቤቶችን መክፈት እንደሚቻል ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ምክረ ሃሳብ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

Recent News
Follow Us