News Detail
Apr 29, 2025
6 views
በአፍሪካ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የትምህርት መሰረተ ልማትን ከመገንባት ባለፈ የመምህራንን አቅም መገንባት እንደሚገባ ተጠቆመ።
"ኢኖቬሽን አፍሪካ 2025" የአፍሪካ የትምህርት፣ የኢኖቬሽና ቴክኖሎጂ እና ክህሎት የሚኒስትሮች ስብሰባ "በ21ኛው ክፍለ ዘመን አፍሪካን ማስተማርና ማብቃት" በሚል መሪ ሀሳብ የፓናል ውይይት ተደርጓል።
በዚሁ ወቅት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ኢትዮጵያ የትምህርት ስርአቱን ለማሻሻልና ጥራትን ለማረጋገጥ ያከናወነቻቸውን ዋና ዋና የሪፎርም ተግባር በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተደረገው ሀገራዊ ሪፎርም የትምህርት ዘርፉን አካታችነት ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት እኩል የሚስተናገዱበት እንዲሆን እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ከለውጡ በፊት የትምህርት ጥራት ችግር እንደነበር ያነሱት ሚኒስትሩ፤ የቅድመ መደበኛ ትምህርት በከተማ ብቻ ተወስኖ ይሰጥ እንደነበርም አንስተዋል፡፡
እንደ ሀገር በትምህርት ዘርፉ በተደረገው ሪፎርም የቅድመ መደበኛ ትምህርትን በማስፋፋት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየተሠራም ነው ተብለዋል።
በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ከ35 ሺህ በላይ መሰረተ ልማት የተሟላላቸው የቅደመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቅሰዋል።
የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት በማሻሻል እና በቂ መሰረተ ልማት የተሟላላቸው ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ረገድ ለተገኘው ውጤት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ነበርም ብለዋል።
ትምህርት ከፍተኛ ሀብት የሚጠይቅ በመሆኑ በመንግሥት አቅም ብቻ የሚሸፈን አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ፤ የሀብት ማሰባሰብ በሁሉም ዜጋ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ተደርጓል ብለዋል፡፡
አክለውም እንደ አፍሪካ የትምህርት ጥራትን በማሻሻል ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ሀይል ለማፍራት የትምህርት መሰረተ ልማትን ከማሟላት ባለፈ የመምህራንን አቅም መገንባት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል ብለዋለ።
በፓናል ውይይቱም የአንጎላ፣ ዩጋንዳ እና ስዋቶ የትምህርት ሚኒስትሮች በትምህር ዘርፍ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ዜጎችን ማፍራት የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ በማድረግ እየሰሩ ያሉትን ስራ አብራርተዋል።
ሚኒስትሮቹ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥና የትምህርት ሥርዓቱን ለመለወጥም ብዙ ጥረት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል ።