News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
May 02, 2025 10 views

ትምህርት ሚኒስቴር ከሚያስገነባቸው 50 ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንዱ የሆነው የአጋ ጢንጠኖ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ተጀመረ።

ሚኒስቴሩ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ሻኪሶ ከተማ የሚያስገነባው አጋ ጢንጠኖ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ተጀምሯል።
ግንባታውን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የኦሮሚያ ክልል በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ሳዳት ነሻ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) አስጀምረውታል።
ትምህርት ዓለም ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን ወሳኝ በመሆኑ የሀገራችንን የትምህርት ሥርዓት ከመሠረቱ በመቀየር ሀገር የሚገነባ ቀጣይ ትውልድ ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
ይህ በሻኪሶ ከተማ የሚገነባው ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በከተማው ያለውን የትምህርት ቤት እጥረት የሚፈታ ይሆናል።
በዚህም የከተማው አስተዳደርና አባገዳዎች ትምህርት ሚኒስቴር ያለውን ችግር በመመልከት ይህንን ትምህርት ቤት ግንባታ በሻኪሶ በማስጀመሩ ምስጋና አቅርበዋል።
የትምህርት ቤቱ ግንባታ ከአስር እስከ አሥራ ሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃልም ተብሏል።
ትምህርት ሚኒስቴር በራሱ ከሚያስገነባቸው ት/ቤቶች በተጨማሪም የ”ትምህርት ለትውልድ'' የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻል ህዝባዊ ንቅናቄ በመላ ሀገሪቱ በማስጀመር ከ80 ቢሊየን ብር በላይ ሀብት በማሰባሰብ የአዳዲስ ትምህርት ቤቶች ግንባታ እንዲሁም የነባር ትምህርት ቤቶች ጥገናና እድሳት እንዲደረግላቸው ማድረጉም በመድረኩ ተገልጿል።
በዚህም የኦሮሚያ ክልል ቡኡራ ቦሩ፣ ኢፋ ቦሩ እንዲሁም አዳሪ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት እና ህብረተሠቡን በማስተባበር በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውም ተብራርቷል።
በተለይም የትምህርት ጥራት ችግርን ከመሠረቱ ለማስተካከል ከ17ሺ በላይ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ከሁለት ሚሊየን በላይ ህፃናት እንዲማሩ መደረጉ የተገለፀ ሲሆን።
ክልሉ በትምህርቱ ዘርፍ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥና በሳይንስና ቴክኖሎጂ የዳበሩ የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎችን ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑም ተጠቅሷል።
በክልሉ በትምህርት ሚኒስቴር አማካኝነት የተጀመሩት ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ጥራታቸውን ጠብቀው በተያዘላቸው ጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ በቂ ክትትልና ድጋፍ ለማድረግ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል።
Recent News
Follow Us