News Detail
May 03, 2025
12 views
በተከታታይ ሦስት ጊዜ በተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና ከ25 በመቶ በታች ውጤት በሚያስመዘግቡ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ እርምጃ እንደሚመወሰድ ተገለፀ። የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ከቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት ጋር ተወያይተዋል።
በዚሁ ጊዜ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ዩኒቨርሲቲዎች ሰው እውቀትና እውነት ፈልጎ የሚመጣባቸው ተቋማት ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች በተፈጥሮ የተሰጡ የአካባቢው ፀጋዎች ላይ ራዕይ ይዘው መሥራት ይገባቸዋል ያሉ ሲሆን ቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲም በማዕድን ላይ ሰፊ ምርምር በማድረግ ህብረተሰቡን ብሎም ሀገርን የሚጠቅም ሥራ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።
አክለውም ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሯቸው ተማሪዎች ብቃት ያላቸውና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግን ዋና ተግባራቸው አድርገው መሥራት አለባቸው፦
በዚህ ረገድ በተከታታይ ሦስት ጊዜ በተመራቂ ተማሪዎች በመውጫ ፈተና ውጤት ከ25 በመቶ በታች ካስመዘገቡ በትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን በኩል እርምጃ እንደሚወሰድ አመላክተዋል።
የዩኒቨርሲቲ አመራሮች በብቃትና በችሎታ እንዲመደቡ እየተደረገ መሆኑን አንስተው አሰራራቸውን ለማዘመንም የዩኒቨርሲቲ አመራሮች ማሰልጠኛ ተቋም ለማቋቋሞ እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሽኔ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲዎች በተሰጣቸው የተልዕኮ መስክ ልየታ መሠረት ትኩረት አድርገው ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።
አክለውም ዩኒቨርሲቲዎች የእውቀትና የሥነ ምግባር ፋና በመሆናቸው ተማሪዎቻቸውን ማብቃት ላይ ትኩረት አድርገው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲን በተመለከተ በትምህርት ሚኒስቴር የሱፐርቪዥን ቡድን በጥንካሬና በክፍት የተለዩትን ጉዳዮች ያቀረቡት ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት የአሰተዳደርና መሠረተ ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ሰለሞን አብርሃ (ዶ/ር) ሲሆኑ።
ዩኒቨርስቲው ብቃት ያላቸውና ተወዳዳሪ የሆኑ ተማሪዎችን በማፍራት ተመራጭ ዩኒቨርስቲ እንዲሆን ራዕይ ይዞ መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል።
የቡሉሆራ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላትም በአካዳሚክ እና በአስተዳደር ረገድ አሉ ያላቸውን ጥያቄዎች አንስተው ሰፊ ውይይት ተደርጓል።