News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
May 01, 2025 9 views

ትምህርት ሚኒስቴር በአለታ ጩኮ ከተማ የሚያስገነባው ሩፎ ዋኤኖ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ ተጀመረ።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ትምህርት ሚኒስቴር በሲዳማ ክልል ደቡባዊ ሲዳማ ዞን አለታ ጩኮ ከተማ የሚያስገነባውን ሩፎ ዋኤኖ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታን አስጀምረዋል።
በከተማ አስተዳደሩ ያለው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንድ ብቻ በመሆኑ ይህ በትምህርት ሚኒስቴር የሚገነባው ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያለውን ችግር በመፍታትና የተማሪ ክፍል ጥምርታውን በማመጣጠን ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ።
ምቹና መሠረተ ልማት የተሟላላቸው ትምህርት ቤቶች መኖር ምቹ መማር ማስተማርን ከመፍጠር ባሻገር ተማሪዎች ትምህርት ቤቶቹን ወደው እንዲመጡም ያደርጋል ተብሏል።
በመድረኩም በደቡባዊ ሲዳማ ዞን የትምህርት ጥራትን ከመሠረቱ ለመፍታት በትምህርት ለትውልድ የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻል ህዝባዊ ንቅናቄ ስታንዳርዳቸውን የጠበቁ 21 የሚሆኑ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው የመማር ማስተማር ሥራ መጀመራቸው ተገልጿል።
በተጨማሪም ከ86 ሚሊየን ብር በላይ ሀብት በማሰባሰብ የነባር ትምህርት ቤቶች ጥገናና እድሳት መደረጉ የተገለፀ ሲሆን ህብረተሰቡ ትምህርትን በባለቤትነት ለመደገፍ የሚያደረገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠይቋል።
የተጀመረው የትምህርት ቤት ግንባታ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ የመማር ማስተማር ሥራ የሚጀምር ሲሆን ግንባታው ጥራቱን ጠብቆ እንዲጠናቀቅ በማድረግ በኩል ኃላፊነቱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ እንዲወጣ የስምምነት ፊርማ ተፈራርመዋል።
ትምህርት ሚኒስቴር በቂ መሠረተ ልማት የተሟላላቸው 50 ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመላ ሀገሪቱ በተመረጡ አካባቢዎች ለመገንባት አቅዶ እየሠራ እንዳለ ይታወቃል።
Recent News
Follow Us