News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
May 01, 2025 11 views

ሁለም ዜጎች እኩል የትምህርት እድል እንዲያገኙ እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ። የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ነገሌ አርሲ ከተማ የኡታ ዋዩ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታን አስጀምረዋል።

በዚሁ ጊዜ የመሠረተ ልማት የተሟላላቸው ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶቾን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እየገነባ መሆኑን ጠቅሰው ዛሬ ግንባታው የተጀመረው ኡታ ዋዩ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንዱ መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም ሁሉም ኢትዮጵያዊያን እኩል የትምህርት እድል እንዲያገኙ በትኩረት እየተሠራ ነው ያሉ ሲሆን፦
ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ሥርዓቱን ለመቀየር በርካታ የሪፎርም ተግባራትን ቀርፆ እየተገበረ ይገኛል ብለዋል።
ሀገሪቱ ከሌላው አለም ጋር ተወዳዳሪ እንድትሆን፤ ብቁ ተወዳዳሪ፣ ክህሎትን የተላበሱና ግብረ ገብነት የተላበሱ ዜጎችን ለማፍራት የሚያስችሉ ሥራዎችም እየተሠሩ መሆኑን አብራርተዋል።
በግንባታ ማስጀመሪያው ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ሳዳት ነሻ በበኩላቸው ትምህርት ሚነስቴር የትምህርት ሥርዓቱን ለመቀየር እየሠራ ያለው ሥራ የሚመሰገን መሆኑን ጠቅሰው ክልሉ ትምህርትን ከመሠረቱ ለመቀየር ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ እስከ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ድረስ ህብረተሰቡን በማሳተፍ በርካታ ትምህርት ቤቶችን መገንባት መቻሉን ጠቅሰዋል።
በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቶላ በሪሶ(ዶ/ር) በበኩላቸው ይህ አካባቢ በርካታ ተማሪዎች ያሉበት በመሆኑ አሁን የሚገነባው ትምህርት ቤት የተማሪ ጥምርታን በማስተካከል ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።
በተለይም ግንባታው እንዲጀመር ቦታ በመዘጋጀትና ካሳ በመክፈል የከተማ አስተዳደሩ ለሠራው ሥራ አመስግነው የትምህርት ቤቱ ግንባታ እስኪጠናቀቅም አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
የትምህርት ቤቱ ግንባታ ስታታንዳርዱን ጠብቆ በአስር ወር ይጠናቀቃል የተባለ ሲሆን ለዚህም በትምህርት ሚኒስቴርና በክልሉ ትምህርት ቢሮ መካከል የስምምነት ፊርማ ተፈርሟል።
Recent News
Follow Us