News Detail
Apr 30, 2025
7 views
ኢትዮጵያ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት በመቅረጽ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን ቴክኖሎጂና ክህሎትን የተላበሱ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት በትኩረት እየሰራች መሆኑ ተገለፀ።
ኢኖቬሽን አፍሪካ 2025 የትምህርት ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ የሪፎርምና የፖሊሲ እርምጃዎች ላይ ያላትን ልምድ አካፍላለች።
በመድረኩ ትምህርት ሚኒስቴርን በመወከል ፓናሊስት የነበሩ የትምህርት ፕሮግራሞችና ጥራት መሻሻል መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ዮሐንስ ወጋሶ የትምህርት ዘርፉን ለመለወጥ እየተወሰዱ ያሉ የሪፎርም ተግባራትን አብራርተዋል።
በዚሁ ጊዜ በትምህርት ሥርዓቱ የነበሩ ችግሮችን በሮድ ማፕ በመለየት ኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲዋን ከመቀየር ጀምሮ ትምህርትን ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ የትምህርት ህግ ማጽደቋን ጠቅሰዋል።
በዚህም ትምህርት ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል ነፃና ግዴታ እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል።
በተጨማሪም የሥርዓተ ትምህርት ለውጥ በማድረግ ትምህርቱን ከቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር የ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን ክህሎትን የተላበሱ ዜጎችን ለማፍራት እየተሠራ መሆኑንም አንስተዋል።
የቱንም ያህል ሥርዓተ ትምህርት ቢቀየር ምቹ የትምህርት ቤት ከባቢን መፍጠር ካልተቻለ ጥራትን ማረጋገጥ አይቻልም ያሉ ሲሆን፤
ይንንም ለማስተካከል የአዲስ የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ዲዛይንና ስታንዳርድ በማዘጋጀት እንዲሁም የትምህርት ለትውልድ የትምህርት ቤት መሠረተ ልማት ማሻሻል ህዝባዊ ንቅናቄን በመላ ሀገሪቱ በማስጀመር ከ80 ቢለየን ብር በላይ የሚገመት ሀብት በማሰባሰብ ከሰባት ሺህ በላይ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ግንባታ እና በርካታ ነባር ትምህርት ቤቶች እድሳት ማከናወን ተችሏል ብለዋል።
አክለውም ሀገር በቀል የትምህርት ቤት ምገባን ተግባራዊ በማድረግ ተማሪዎች ምግብ እያገኙ መደረጉን አብራርተዋል።
Innovation Africa 2025 በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በመዲናችን አዲስ አበባ እየተካሄደ እንዳለ ይታወቃል።