News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Feb 01, 2023 4K views

"በኢትዮጵያ አዲስ ከተቀረጸው ስርዓተ ትምህርት ታንዛኒያ ጠቃሚ ግብዓት አግኝታለች " የታንዛኒያ የትምህርት ፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ቋሚ ምክትል ሚኒስትር

ጥር 24/2015 ዓም (ትምህርት ሚኒስቴር) የታንዛኒያ የትምህርት ፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ልዑካን ቡድን በትምህርት ሚኒስቴር የልምድ ልውውጥ ጉብኝት አድርጓል ።
12 አባላት ያሉት የታንዛኒያ የልዑካን ቡድን በቅድመ መደበኛ ፣ በሁለተኛ ደረጃ ፣ በቴክኒክና ሙያና በዩኒቨርስቲዎች በመዘዋወር ምልከታ አድርጓል።
ልዑካን ቡድኑን የመሩት የታንዛኒያ ሪፐብሊክ ቋሚ ምክትል የትምህርት፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ጀምስ ኤፒፈን ጋብርኤል ሞድ በጉብኝቱ ወቅት በኢትዮጵያ አዲስ ከተቀረጸው ስርዓተ- ትምህርት አገራቸው በርካታ ጠቃሚ ልምዶችን እንዳገኘች ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅት አገራቸው ታንዛኒያ የስርዓተ ትምህርት ማሻሻያና ክለሳ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ለአገር በቀል ዕውቀቶች ፣ ለተግባርና ሙያ ( ክህሎት ) ትኩረት የሰጠ መሆኑንን ተናግረዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የስርዓተ ትምህርት ማበልጸጊያ መሪ ስራ አስፈጻሚ ቴዎድሮስ ሸዋርገጥ (ዶ/ር) በበኩላቸው ነባሩ ስርዓተ ትምህርት መለወጥ ያስፈለገው በንድፈ ሀሳብ የታጨቀና የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ በመሆኑ ነው ብለዋል።
አዲሱ ስርዓተ ትምህርት አገራዊ ፍላጎትን ያገናዘበ በቴክኖሎጂ ፣ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚያዊ ውድድር በመፍጠር ውጤታማ የሚያደርግ መሆኑንም ለልዑካን ቡድኑ አስረድተዋል።
በስርዓተ ትምህርቱ ዝግጅት ላይም የመጻህፍት ዝግጅት ፣ የትምህርት ጥራት ማረጋገጥና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ የመስራት ልምድም መገኘቱን ዋና ስራ አስፈጻሚው ጨምረው ገልጸዋል።
ትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ስርዓተ-ትምህርት ክለሳ በማድረግ በሙሉ እና በሙከራ ትግበራ ላይ እንደሚገኝ ይታወሳል።
Recent News
Follow Us