News Detail
Oct 18, 2022
2.3K views
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአዲስአበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ፈተና አስጀመሩ።
ጥቅምት 08/2015ዓም.(ትምህርት ሚኒስቴር) የ12ኛ ክፍል የ2ኛው ዙር የተፈጥሮ ሳይንስ ፈተና በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች መሠጠት ተጀመሯል።
የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ፈተናውን በአዲስአበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው አስጀምረዋል።
የትምህርት ሚንስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው መርሃ ግብር መሰረት ፈተናው ያለምንም ችግር በሁሉም ፈተና ጣቢያዎች በሰላም እንደተጀመረ ገልፀዋል።
ፕሮፌሰሩ አክለውም " ከመጀመሪያው ዙር ተምረን በርካታ ነገሮችን ስላስተካከልን የዚህ ዙር ፈተና በተጀመረበት መልኩ እንደሚጠናቀቅ ተስፋ እናደርጋለን" ብለዋል።
ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ እንዲፈተኑ መደረጉ በትምህርት ስርዓቱ ያለውን የሞራል ስብራት የሚጠግን መሆኑን ገልፀው ይህ ከፍተኛ ትርጉም እንዳለው ማህበረሰቡም በሚገባ የተረዳና የደገፈው በመሆኑ በጣም ደስተኞች ነን ብለዋል።
የ2ኛው ዙር ፈተና ከጅምሩ ምንም ችግር አላየንበትም ያሉት ሚኒስትሩ በቀጣይ በፈተና ስርዓቱ ያሉ ችግሮችን ሙሉ በሙሉ ቀርፈን ወደ አዲስ ምእራፍ እገባለን ብለዋል።
የአዲስአበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ከአዲስአበባ እና ከኦሮሚያ ክልል የመጡ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስፈተነ ይገኛል።
የ2ኛው ዙር የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ፈተና ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ አራት ቀን የሚሰጥ ይሆናል።