News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Oct 26, 2022 3.1K views

የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና አሰጣጥ አፈጻጸም የተሳካ ነበር ፦ ትምህርት ሚኒስቴር ።

የትምህርት ሚኒስቴር የ2014ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና አሰጣጥ የተሳካ እንደነበረ አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ በ2014ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና አሰጣጥ ሂደት ዝርዝር መረጃዎች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ በሁለት ዙር ሲሰጥ የነበረው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በታቀደው መሰረት መሰጠቱን እና የነበረው ሂደትም ውጤታማ እንደነበር ገልፀዋል።
ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም የፈተና አስተዳደር ስርዓቱ አደጋ ውስጥ ወድቆ መቆየቱን እና የፈተና ስርዓቱም የፓለቲካ ጥቅም ላይ ሲውል መቆየቱንም ገልፀዋል።
በ2014ዓ.ም ሀገር አቀፍ ፈተና በአጠቃላይ ከ 900ሺህ በላይ ተፈታኞች ፈተናውን የወሰዱ ሲሆን ይህም ከዚህ ቀደም ከነበረው የተፈታኝ ቁጥር በእጅጉን እንደሚልቅ ተገልጿል።
በአጠቃላይም ከተመዘገቡት ተማሪዎች ውስጥ 98.8 በመቶ ተማሪዎች ተፈትነዋል፡፡ ፈተናውን ለማስፈፀምም ከ25ሺህ በላይ ፈተና አስፈፃሚዎች እና ከ 6ሺህ በላይ የፀጥታ ሀይሎች ለፈተናው መሰማራታቸው ተሰማርተዋል።
በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ያጋጠመው አደጋ እና ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ተፈታኞች ያጋጠመዉ ትራፊክ አደጋ ፣ በመቅደላ አምባ፣ ደብረማርቆስ፣ ባህር ዳር እና ደብረታቦር ዩኒቨርስቲዎች ላይ 12ሺ 993 ተማሪዎች አንፈተንም ብለው ፈተና ትተው መውጣታቸው በፈተና ወቅት ያጋጠሙ ክስተቶች መሆናቸውን ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
በፈተና ወቅትም በ33 የፈተና ጣቢያዎች 53 ተፈታኞች ስልክ ይዘው ለመግባት የሞከሩ ሲሆን ፈተና አስፈፃሚዎችንም በኩል የማዋከብ እና የፈተና ስነምግባር ግድፈቶች መታየታቸውን እና በፈታኞችም በኩል የፈተና ስርዓትን ያለመከተል ተግዳሮት እንደነበሩም ተገልጿል።
በመግለጫው በጤና እና ማህበራዊ ምክንያት ፈተናውን ያልወሰዱ ተማሪዎች ከ2015 መደበኛ ተፈታኞች ጋር ፈተናውን እንደሚወስዱ የተገለፀ ሲሆን ፈተናውን ጥለው የወጡ ተማሪዎች ግን በመንግስት በኩል ሌላ እድል እንደማይሰጣቸዉ ነገር ግን በግል ፈተናውን መውሰድ እንደሚችሉ ተገልጿል።
በፈተና ጣቢያው ውስጥ የወለዱ ተፈታኞችም በአንድ ወር ውስጥ በሚሰጥ ፈተና ይስተናገዳሉ።
ሚኒስትሩ ለፈተናው አሰጣጥ ሂደት ስኬታማነት የበኩላቸውን ለተወጡ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የ2014 ፈተና አሰጣጥ በትምህርት ስርዓቱ ላይ ያለውን ስብራት ለማከም አንድ እርምጃ ከመሆኑም ባሻገር ተግዳሮቶችን ወደ አቅም ለመቀየር እድል የሰጠም እንደነበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ገልፀዋል።
Recent News
Follow Us