News Detail

የሀገር ውስጥ ዜና
Jun 02, 2021 230 views

የትምህርት ሚኒስቴር ለቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በትምህርት ዘርፉ ላይ እያበረከቱት ላለው አስተዋጾ እውቅና ሰጠ።

የትምህርት ሚኒስቴር ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በተለያዩ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶችን በማስገንባት በትምህርት ዘርፉ ላይ እያበረከቱት ላለው አስተዋጾ እውቅና ሰጥቷል።
በእውቅና ፕሮግራሙ ላይ ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ለሀገር ለውጥ ትምህርት ትልቅ ሚና እንዳለው ተገንዘበው ያደረጉት ስራ ያስመሰግናቸዋል ብለዋል።
"መሰረተ ድንጋይ ማስቀመጥ ሳይሆን ሰርቶ መጨረስን ያሳዩ እና ድምፃቸውን አጥፍተው ብዙ የሰሩ ጀግና ሴት ናቸው" ብለዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ.) በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፉ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል የትምህርት ቤቶች እጥረት አንዱ መሆኑን ገልፀው ቀዳማዊት እመቤት ይህንን ተገንዝበው ትምህርት ቤቶችን በማስገንባት እያበረከቱት ላለው አስተዋጾ ምስጋና አቅርበዋል።
የትምህርት ቤቶቹ መገንባት የትምህርት ቤት እጥረቶችን ከመቀነስም ባሻገር ተማሪዎች እረጅም እርቀት ሳይጓዙ በአካባቢያቸው ትምህርትን እንዲያገኙ የሚያድረግ መሆኑንም ተናግረዋል።
በእውቅና ፕሮግራሙም ላይ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጀላቸውን ሽልማት አበርክተዋል።
የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት አርዕያን በመከተል ሌሎች የመንግስት እና የግል ድርጅቶች እንዲሁም ባለሀብቶችም የትምህርት ዘርፉን እንዲደግፉ ጥሪ ቀርቧል።
ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በሁሉም ክልሎች 20 ትምህርት ቤቶችን አስገንብተው በማጠናቀቅ አገልግሎት እንዲሰጡ አድርገዋል።
Recent News
Follow Us