News Detail
Jan 05, 2021
614 views
ሀገር በቀል የግብረ-ገብ፣ የዜግነትና የሰላም ዕሴቶችን ያካተተ ስርዓተ-ትምህርት ለማዘጋጀት እየተሰራ ነው፡-ትምህርት ሚኒስቴር
በስነ-ምግባር የታነፀ ዜጋ ለመፍጠር ሀገር በቀል የግብረ-ገብ፣ የዜግነትና የሰላም ዕሴቶችን ያካተተ ስርዓተ-ትምህርት ለማዘጋጀት ትምህርት ሚኒስቴር አውደ ጥናት እያካሄደ ነው።

አውደ ጥናቱ በስርዓተ ትምህርቱ ውስጥ የሀገር በቀል የግብረ-ገብ፣ ዜግነትና የሰላም ዕሴቶች ላይ ግብዓት መሰብሰብ ዓላማ ያደረገ ነው።
የሚሻሻለው የግብረ-ገብና ዜግነት ትምህርት ከ1ኛ -6ኛ ክፍል የግብረ-ገብ ትምህርት እንዲሁም ከ7ኛ ክፍል ጀምሮ ደግሞ የዜግነት ትምህርት ተብሎ የሚዘጋጅ ይሆናል፡፡
ለሚዘጋጀው የግብረ-ገብና ዜግነት ትምህርት ስርዓተ ትምህርት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ከወሎ ዩኒቨርስቲ፣ ከአዲስ ኪነ-ጥበባት የባህል ማዕከል፣ ከኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባዔና ከሌሎች ተቋማት የመጡ ከፍተኛ ምሁራን፣ተመራማሪዎች፣ የፍልስፍናና የሀይማኖት ሰዎች ጥናታዊ ፅሁፎቻቸውን አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በመድረኩም ከክልል ትምህርት ቢሮ ፣ ከመምህራን ማህበር፣ ከመምህራን ኮሌጆች፣ ከሰብዓዊ መብት ኮሚሺን፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ፣ ከሴቶችና ህጻናት ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድረሻ አካለት የተውጣጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል፡፡
ከስርዓተ-ትምህርቱ ችግሮች መካከል የግብረ-ገብ ትምህርትን በሚፈለገው ልክ አካቶ አለመያዙ መሰረታዊ ችግር ሆኖ በትምህርትና ስልጠና ፍኖተ-ካርታው ላይ መገለፁ የሚታወስ ነው፡፡