News Detail

National News
Dec 27, 2025 23 views

የትምህርት ሚኒስቴር አጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ በጂግጂጋ ፌዴራል ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ላይ በመገኘት መልዕክት አስተላለፉ።

የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ከማረጋገጥ አንጻር ትልቅ ተስፋ ከተጣለባቸው የፌደራል አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ የሆነው የጂግጂጋ የፌዴራል አዳሪ ትምህርት ቤት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚንስቴር አጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ ለተማሪዎችና መምህራን እንዲሁም ለአጠቃላይ የት/ቤቱ ማህበረሰብ መርሃ ግብሩን በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም መንግስት የትምህርት ጥራት፣ አግባብነትና ተደራሽነትን ከማረጋገጥ አንጻር በርካታ ስራዎችን እየሰራ ነው ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታዋ በዚህ የፌደራል አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተገኛችሁ ተማሪዎች፣ መምህራን እና የትምህርት ቤት አመራሮች ታሪካዊ በሆነው መርሃ ግብር የመጀመሪያዎቹ ተዋንያን በመሆናችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
አያይዘውም ተማሪዎች ዓላማቸው ላይ ትኩረት በማድረግ በትምህርታቸው ብቻ ሳይሆን በስነ-ምግባርም ምሳሌ የሚሆኑ ዜጎች እንዲሆኑ፤ መምህራንና የትምህርት ቤት አመራሮች እንደ ቤተሰብ ሆነው በታላቅ ሃላፊነት ተማሪዎችን በማገዝ ብቁ ዜጎችን እንዲያፈሩ አደራ ብለዋል።
ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ከዚሁ ጋር በማያያዝም እስካሁን በጂግጂጋ ዩኒቨርሲቲ እና በክልሉ ትምህርት ቢሮ በኩል ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተናገድና ግብዓቶችን በማሟላት ረገድ እየተከናወኑ ያሉ ጥረቶች አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም የተጀመሩ ስራዎችን በተጠናከረ ሁኔታ በማስቀጠል ክፍተቶች እየተሞሉ ለመማር ማስተማር ስራው ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ መሄድ እንዳለበት አሳስበዋል።
በማስጀመሪያው መርሃ ግብር ላይ የሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ክቡር አቶ መሃመድ አደን እና የጂግጂጋ ዩኒቨርሲቲ ፔሬዘዳንት ዶ/ር ሠይድ መሃመድ በመገኘት ለትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
Recent News
Follow Us