News Detail
Sep 03, 2025
19 views
በትምህርት ሚኒስትሩ የተመራ የልዑካን ቡድን በቺሊ ሳንቲያጎ በተካሄደው አለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ተሳትፏል።
ይህ አለም አቀፍ ጉባኤ በቺሊ ፕሬዚዳንት ገብርኤል ቦሪቼ እና በዩኔስኮ ዋና ዳይሬክተር ኦድሪ አዙላይ አማካኝነት የተመራ ሲሆን በሀገራት ደረጃ የኤሰ ዲ ጂ 4 እድገትን ለማፋጠን ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
በዚህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ አፍሪካን በመወከል የኢትዮጵያ እና የኮትዲቫር የትምህርት ሚኒስትሮች ተሳትፈዋል።
በዚሁ ጊዜ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ባስተላለፉት መልዕክት በ2030 የትምህርት ዘላቂ ግብን ለማሳካት በሁሉም ሀገራት በተለይም በታዳጊ ሀገራት በርካታ ሥራ መስራት ይጠበቃል ብለዋል።
አክለውም የአፍሪካ ሀገሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ የመጣውን የውጭ እርዳታ መተማመናቸውን በመተው ከችግሮቻቸው ለመውጣት ህብረተሰቡን በማስተባበር በራስ አቅም መንቀሳቀስ ዘላቂ ልማትና እድገት ለማምጣት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ እየሰራች ያለውን ሥራ ያነሱት ክቡር ሚኒስትሩ በተለይም በትምህርት ለትውልድ የትምህር ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻል ንቅናቄ ፣ በቅድመ መደበኛ ትምህርት፣ በትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ በትምህርት ቤት የተማሪዎች ምገባ መርሃግብር ረገድ የተገኙ ስኬቶችን በመድረኩ አብራርተዋል።
በዚህ አለም አቀፍ ጉባኤ የ28 ሀገራት የትምህርት ሚኒስትሮች ፣ ኤጀንሲዎች፣ የሼርፓ ቡድን ከፍተኛ የቴክኒክ ቡድን ተወካዮች ተሳትፈዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ክቡር ሚኒስትሩ ከጉባኤው በተጓዳኝ "በመምህራን ላይ የዓለም ጉባኤ" በሚል ርዕስ በተካሄደ መድረክ ላይም ተሳትፈዋል።