News Detail
Dec 16, 2024
244 views
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕፌሰር ብርሃኑ ነጋ በደቡብ ሱዳን መንግስት የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ከተመራ ልዑካን ቡድን ጋር ተወያዩ።
የትምህርት ሚኒስትሩ በደቡብ ሱዳን የከፍተኛ ትምህርት ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ገብሬላ ቻንግሰን ቻንግ የተመራ ልዑክን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ዜጎች እየሰጠች ባለችው የትምህርት እድልና ባጋጠሙ ችግሮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በዚሁ ጊዜ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕፌሰር ብርሃኑ ነጋ የኢትዮጵያ መንግስት ለደቡብ ሱዳን ዜጎች ባለፉት አመታት በርካታ የትምህርት እድል ሲሰጥ መቆየቱን አንስተዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር በትምህርት ሥርዓቱ ተወዳዳሪ፣ ብቁ እና ክህሎት ያላቸውን ተማሪዎች ለማፍራት እየሰራቸው ያሉ ሪፎርሞችን ለሉካን ቡድኑ ያብራሩ ሲሆን የነጻ የትምህርት እድል የተሰጣቸው ተማሪዎችም ሲመረጡ ይህንን ታሳቢ ያደርጉ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በተለይም የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂ ተማሪዎች መውጫ ፈተናን እንዲሁም የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች የመግቢያ ፈተናን እንደሚወስዱ አውቀው ሲመረጡ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ጠንካራ መግቢያ ፈተና መስጠት እንዳለባቸውና ተማሪዎች ትምህርታቸውን በውጤታማነት ማጠናቀቅ እንደሚገባቸውም አብራርተዋል።
የደቡብ ሱዳን የከፍተኛ ትምህርት ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ክቡር ገብሬላ ቻንግሰን በበኩላቸው ከሁለት ዓመት በፊት የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት በጥሩ ሁኔታ እየተፈጸመ መሆኑን ገልጸው የኢትዮጵያ መንግስት ለደቡብ ሱዳን ዜጎች በተሰጠው የነጻ ትምህርት እድልና እየተደረገላቸው ባለው ድጋፍ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብን አመስግነዋል።
አክለውም ኢትዮጵያ ጥራትና ብቃት ያላቸውን ተማሪዎች ለማፍራት እየሰራች ያለውን ሥራ አድንቀው በደቡብ ሱዳንም የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ጠንካራ እንዲሆን በማድረግ በኢትዮጵያ የትምህርት እድል የሚሰጣቸው ተማሪዎችም የተሻለ ውጤትና ብቃት ያላቸው እንዲሆኑ እንሰራለን ብለዋል።
ሁለቱ ሀገራት ባደረጉት ውይይትም የትምህርት እድል የተሰጣቸው ተማሪዎች ከቪዛ፣ ከመኖሪያ፣ ከትራንስፖርት እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲ ቆይታ ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን መፍታት በሚቻልባቸው ጉዳይ ላይ ከተወያዩ በኋላ የየድርሻቸውን ለመወጣት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።