News Detail
Nov 07, 2024
66 views
የትምህርት ሚኒስቴር ከራሽያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችለውን የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ።
የትምህርት ሚኒስቴር ከራሽያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ በትብብር ለመስራት የሚያስችለውን የስምምነት ሰነድ ተፈራርሟል።
የተፈረመው ስምምነት ሰነድ በእኩልነት፣ በጋራ ተጠቃሚነትና ውጤታማነት መርህ ላይ በመመስረት ሁለቱ ሀገራት በከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸው መሆኑ ተመላክቷል።
በስምምነቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር በትብብር የሚሰሩበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ያለመ መሆኑ በዚሁ ወቅት ተገልጿል።
በመግባቢያ ስምምነት ፊርማ ሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ራሽያ ከኢትዮጵያ ጋር የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነት እንደነበራት አንስተው በተለይም በአሁኑ ወቅት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት ብቃት ያላቸውና አለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎችን ለማፍራት በአጠቃላይና ከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ በርካታ የሪፎርም ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን በኢትዮጵያ ያራሽያ አምባሳደር ለተመራው ልኡካን ቡድኑ አብራርተዋል።
ክቡር ሚኒስትሩ አያይዘውም እስካሁን ድረስ ራሽያ ለኢትዮጵያ ተማሪዎች የሰጠችውን ድጋፍ አመስግነው በቀጣይም በሀገራችን የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የተጀመረው ሪፎርም የበለጠ ውጤታማ እንዲሆንና ከፍተኛ ብቃት ያለው የሰው ሃይል ስለሚፈልግ ድጋፏን አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል።
የራሽያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ምክትል ሚኒስትር በበኩላቸው ስምምነቱ በአለም አቀፍ ትብብር መሰረት ሁለቱ ሀገራት በከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ በጋራ የሚሰሩበትንና ልምድ የሚለዋወጡበትን ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም በትምህርት እድል፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል የልምድ ልውውጥ፣ የመማሪያና ማስተማሪያ ግብዓቶችን መጋራት፣ ሳይንሳዊ ጥናቶችን በጋራ የመስራትና ሌሎች የአቅም ማጎልበቻ ሴሚናሮች በጋራ ለማካሄድ የሚያስችል ስምምነት መሆኑንም ጠቁመዋል።
በመድረኩ የብሪክስ አባል ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች ትብብር፣ ዩኒቨርሲቲዎች በደረጃ የሚቀመጡበት (Rating System) እንዲሁም የድጋፍ ሥርዓት ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ይህም በዩኒቨርሲቲዎች መካከል ልምድ በመለዋወጥ ረገድ መልካም እድል ይፈጥርላቸዋል ተብሏል።
ስምምነቱን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና የራሽያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ምክትል ሚኒስትር የተፈራረሙ ሲሆን ይህን ስምምነት ወደ ተግባር ለማስገባት በሁለቱም ሀገራት በኩል የቴክኒካል ቡድን ተቋቁሞ ወደስራ እንደሚገባ ተገልጿል።