News Detail

National News
Apr 29, 2024 1.1K views

የትምህርት ለትውልድ የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻል ህዝባዊ ንቅናቄ ግለቱን ጠብቆ ማስቀጠል እንደሚገባ ተጠቆመ።

በትምህርት ለትውልድ የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻል ህዝባዊ ንቅናቄ ከ25.3 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ሀብት ማሰባሰብ መቻሉም ተገልጿል።
ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ የተጀመረውን የትምህርት ለትውልድ የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻል ህዝባዊ ንቅናቄ ግለቱን ጠብቆ ማስቀጠል እንደሚገባ አጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ ጠቁመዋል።
ትምህርት የሁሉም መሠረት እንደሆነ ያነሱት ሚኒስትር ደኤታዋ በትምህርት ስርዓቱ ለሚቀጥለው ትውልድ የሚሆን መሠረት ለመጣል ጠንክሮ መሥራት ይገባል ብለዋል።
በዚህም የትምህርት ስብራቱን ለማከም የሚያስችል አሻራ መጣልና ለውጥ ማምጣት እንደሚያስፈልግም ገልፀው አሁን በትምህርት ዘርፉ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተጀመሩ ሥራዎችን የበለጠ ለማላቅ በበለጠ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት አመራሮቹ እንዲሰሩም አሳስበዋል።
በትምህርት ለትውልድ መሠረተ ልማት ማሻሻል ህዝባዊ ንቅናቄ በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አሰተዳደሮች ከ25.3 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ሀብት ማሰባሰብ መቻሉም ተገለጿል።
በትምህርት ዘርፉ የተካሄደው የትምህርት ለትውልድ የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻል ንቅናቄ ህብረተሰቡ በትምህርት ላይ ያለውን የባለቤትነት ሚና በትክክል ያረጋገጠና ለሌሎች ሴክተሮችም ተሞክሮ መሆን እንደሚችል በመድረኩ ተነስቷል።
የትምህርት ሚኒስቴር ሱፐርቪዥን ቡድን በክልሎች ያደረገው ምልከታ ሪፖርትም በመድረኩ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የሱፐርቪዥኑ ዓላማ መደጋገፍ የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን በሱፐርቪዥኑ የታዩ መልካም አፈፃፀሞችን ማጠናከር እንዲሁም የታዩ ክፍተቶችን ደግሞ በቀጣይ በዕቅድ አካቶ ለመስራት እድል የሚፈጥር ነውም ተብሏል።