News Detail
Mar 06, 2023
2.2K views
የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለጋሞ ባይራ አዳሪ ትምህርት ቤት ግብዓት ለማሟላት እየሰራ ነው።
የካቲት 27/2015ዓም .(የትምህርት ሚኒስቴር ) የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከ16 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለጋሞ ባይራ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የትምህርት ግብዓቶችን የሟሟላት ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡
የጋሞ ባይራ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በጋሞ ልማት ማህበር ተነሳሽነት ተጀምሮ ግንባታው በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ወደ ስራ ገብቷል፡
በዚህም 2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የመጀመሪያዎቹን 214 የ9ኛ ክፍል ተማሪዎችን ከሁሉም ትምህርት ቤቶች በ8ኛ ክፍል ውጤታቸው መሰረት በመመልመል የመማር ማስተማር ስራ ጀምሯል።
የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክተር ተክሉ ወጋየሁ( ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው ከ16 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ቤተ-መጽሐፍት፣ ቤተ-ሙከራዎችን እና አይ ሲቲ ክፍሎችን የማደራጀትና አስፈላጊ ግብዓቶችን የሟሟላት ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም የትምህርት ቤቱ መምህራንን ብቃትን መሰረት በማድረግ ከመመልመል ጀምሮ አስፈላጊውን የሙያ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልፀዋል፡፡
የእንደዚህ አይነት አዳሪ ትምህርት ቤቶች መኖር ተማሪዎች ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩና ከቴክኖሎጂ ጋር እንዲተዋወቁ ያደርጋቸዋል ያሉት ዳይሬክተሩ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ረገድም የላቀ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ከታች ጀምሮ መስራት እንደሚገባ ጠቁመው ዩኒቨርሲቲው ትምህርት ቤቱ በደንብ እስኪደራጅና የመጀመሪያዎቹን ተማሪዎች 12ኛ ክፍል አድርሶ እስኪያስፈትን ድረስ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያድርግም ተናግረዋል፡፡
ተማሪዎችም የማደሪያ አገልግሎትን ጨምሮ የምግብና የመማሪያ ቁሳቁስ በልማት ማህበሩ አማካኝነት እንደሚቀርብላቸውም ተገልጿል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ሞዴል እና አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ሁሉም ባለድርሻ አካል የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡
Recent News
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምግብ ሜኑ ተመሳሳይ እንዲሆን ተወሰነ።
Dec 09, 2024
የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎትን ለማሳደግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ።
Dec 07, 2024