News Detail
May 21, 2026
45 views
በአጣዬ ከተማ በትምህርት ሚኒስቴር ድጋፍ የተገነባ የአጣዬ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ተመረቀ፤
በትምህርት ሚኒስቴር ድጋፍ በአጣዬ ከተማ የተገነባው የአጣዬ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማሪያ ክፍል ማስፋፊያ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
ትምህርት ሚኒስቴር ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ያስገነባው ይህ ፕሮጀክት ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን እና ዘመናዊ መፀዳጃ ቤቶችን ያካተተ ሲሆን የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች፣ የአካባቢው አስተዳደር፣ የትምህርት ዘርፍ ኃላፊዎች እና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በይፋ ተመርቋል።
የግንባታ ፕሮጀክቱ 10 ዘመናዊ የመማሪያ ክፍሎችን ያካተተ ሲሆን፣ ለወንድና ለሴት ተማሪዎች የተለያዩ መፀዳጃ ክፍሎችን ይዟል።
ፕሮጀክቱ በአካባቢው የትምህርት ተደራሽነትን እና ምቹ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም ተገልጿል።
በተጨማሪም በ“ትምህርት ለትውልድ” የትምህርት ቤቶች መሰረተ ልማት ማሻሻል ንቅናቄ የትምህርት ማህበረሰቡን፣ የቀድሞ ተማሪዎችን፣ ባለሃብቶችን መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማስተባበር በመላ ሀገሪቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የአዳዲስ ትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ የነባር ትምህርት ቤቶች ጥገና እና የትምህርት ተቋማት መሰረተ ልማት ማሻሻያ ሥራዎች በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝ ይታወቃል።
ትምህርት ሚኒስቴር በሁሉም አካባቢዎች ፍትሃዊና ሁሉን አቀፍ ጥራት ያለው ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።