News Detail

National News
Feb 09, 2026 42 views

መጪዎቹ ስድስት ወራት ከ1200 በላይ የሚሆኑ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ለመገንባት መታቀዱ ተገለፀ። እነዚህ ትምህርት ቤቶች እንደ ሀገር ምንም ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በሌላቸው ወረዳዎችን የሚገነቡ ናቸው።

የትምህርት ሚንስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በቀሪ ስድስት ወራት የሚከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ ለክልልና ከተማ መስተዳድር ትምህርት ቢሮ ሀላፊዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት የትምህርት ሚኒስቴር ከአጋር ድርጅቶች ባገኘው ድጋፍ በመላው ሀገሪቱ በሚገኙና ምንም ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በሌላቸው 626 ወረዳዎች ውስጥ አንድ አንድ ትምህርት ቤት የሚገነባ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህ ሀገራዊ ፕሮጀክትም ተጠቃሚ የሚሆኑ ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የትምህርት ሚኒስቴር ባገኘው ድጋፍ በየወረዳው በሚገነባው ትምህርት ቤት ተመሳሳይ ሌላ ት/ቤት እንዲገነቡ የሚጠበቅባቸው በመሆኑ በቀጣይ 6 ወራት በሀገር አቀፍ ደረጃ አዲስ የሚገነቡት ት/ቤቶች ቁጥር ከ1200 በላይ እንደሚሆን ሚንስትሩ አብራርተዋል።
በዚህም የትምህርት ቤቶቹ ዲዛይን ተሰርቶ እየተጠናቀቀ መሆኑን ገለፀው በቀጣይ ከክልሎች ጋር በመሆን ኮንትራክተሮችን በመለየት ግንባታው በፍጥነት እንደሚጀመርም አብራርተዋል።
ፕሮጀክቱ ትምህርት ሚኒስቴር ትምህርትን ለሁሉም ዜጎች በሁሉም አካባቢ በፍትሃዊነትና በጥራት ተደራሽ ለማድረግ የሚያደርገው ጥረት አካል መሆኑን ሚንስትሩ አያይዘው ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት መንግስት ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት በተለይም ህፃናትን ከታች ጀምሮ በእውቀትና በስነ ምግባር በመቅረፅ ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት በሰጠው ልዩ ትኩረት ከ34 ሺ በላይ ትምህርቤቶችን ገንብቷል።
Recent News
Follow Us