News Detail
Jan 17, 2026
63 views
በትምህርት ዙሪያ በምንም መልኩ በድሃና በሀብታም መካከል ልዩነት እንዳይኖር በሁሉም አካባቢዎች ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች እየተሰሩ መሆኑ ተገለፀ ። በጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ የተገነባው ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመርቋል።
ትምህርት ሚኒስቴር ከሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ያስገነባው የሳውላ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ በህ/ተ/ም/ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ ተስፋዬ ቤልጅጌ(ዶ/ር) እና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ መርቀውታል።
በዚሁ ጊዜ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንደ ሀገር በትምህርት ዙሪያ በድሃና ሀብታም መካከል በምንም መልኩ ልዩነት መኖር የለበትም በሚል የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል ዜጎች ፍትሃዊና ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በዚህም ተማሪዎች ትምህርት ቤቶቻቸውን ወደውና ፈልገው እንዲመጡ የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት ለማሻሻል በትምህርት ለትውልድ ህዝባዊ ንቅናቄ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
እንደ ሀገር በአዲሱ የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ዲዛይን መሠረት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች 50 ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰው ይህ ዛሬ የተመረቀው ትምህርት ቤት አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
አክለውም እንደ ከዚህ ቀደሙ የመሠረት ድጋይ አስቀምጦ መሄድ ቀርቷል ያሉት ሚኒስትሩ በገባነው ቃል መሠረት በአጭር ጊዜ ግንባታው ተጠናቆ ተመርቋል፤ ይህም ትምህርት ላይ የሚሰራው ሥራ ከፖለቲካ በፀዳ መልኩ በጋራ የምንሰራው ሥራ ነውም ብለዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በበኩላቸው የተሳካ የሀገረ መንግስት ግንባታ ከትውልድ ግንባታ ተለይቶ የሚታይ አይደለም፤ በዚህም ብቃት ያላቸው ተወዳዳሪ የሆኑና በቴክኖሎጂ የታነፁ ዜጎችን ለማፍራት መንግስት ከታች ጀምሮ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው የሀገራችን የትምህርት ሥርዓት የገጠመው ስብራት ለውጥ ያስፈልገዋል በሚል ትምህርት ሚኒስቴር እየወሰዳቸው ባለው እርምጃ የተመዘገቡ ለውጦች እውቅና የሚሰጣቸው መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ከምንም በላይ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻልና ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች በሁሉም አካባቢዎች እንዲኖሩ እየተሰራ ያለው ሥራ የሁሉንም ትብብር የሚጠይቅ መሆኑን ገልፀዋል።
ይህ ትምህርት ቤት በትምህርት ሚኒስቴር ዲዛይን መሠረት በጥራትና ፍጥነት የተገነባ በመሆኑ ሌሎች በክልሉ ለሚገነቡ ትምህርት ቤቶችም ሞዴል ሆኖ እንደሚያገለግል ተናግረዋል ።
በመድረኩም ትምህርት ቤቱ ለተማሪዎች ምቹ ሆኖ እንዲቀጥልና አስፈላጊው መሠረተ ልማት እንዲሟላለት የዞኑና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።