News Detail
Dec 26, 2025
12 views
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የወሊሶ ፌዴራል ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማር ማስተማር ሥራ የማስጀመር ሥነ ሥርዓት ተካሄደ።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ፣ የትምህርት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ክንደያ ገ/ህይወት፣ የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) እና የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተው አስጀምረዋል።
በዚሁ ጊዜ የትምህር ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት ብቁ፣ ተወዳዳሪና ለወደፊት ለሀገሪቱ ጠንካራ መሪ ለማውጣት ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን በማቋቋም ከመላ ሀገሪቱ ተማሪዎችን በመቀበል ዛሬ ትምህርት የማስጀመሪያ ፕሮግራም አካሂደናል ብለዋል።
ትልቅ ስልጣኔ የነበራትና ትልቅ ሀገር መሆን የሚገባት ሀገር የምትበላውን የምትለምን ሀገር ሆና ወደ ኋላ ቀርታለች ያሉት ሚኒስትሩ።
ባለፉት የለውጥ አመታት በትንሹ በትልቁ ከመባላት ወጥተን እንዴት ሀገራችንን መለወጥ እንችላለን የሚለውን በማሰብ በትምህርት ሥርዓቱ ጠንካራ ተወዳዳሪና ብቃት ያላቸው ልጆችን ለማፍራት የሚያስችሉ ሥራወች እየተሰሩ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የሀገርን እድገት ማረጋገጥ የሚቻለው ጥራት ያለው ትምህርትን በፍትሃዊነት ለሁሉም ዜጎች ማድረስ ሲቻል በመሆኑ በገጠርም ሆነ በከተማ ሁሉም ዜጋ ጥሩ የትምህርት ዕድል እንዲያገኝ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም በዚህ ትምህርት ቤት የመማር እድል ያገኛችሁ ተማሪዎች በትምህርትና በእውቀት ብቻ ሳይሆን ሥነ ምግባር የተላበሳችሁ፣ ከስንፍና የተላቀቃችሁ፣ ሌላውን በመርዳት ሰው እንድትሆኑ እንፈልጋለንም ብለዋል።
ተማሪዎች ልዩ ተሰጥኦ ያላችሁ ልጆች መሆን አለባችሁ ያሉት ሚኒስትሩ እናንተ ከመላው ኢትዮጵያ የመጣችሁ በመሆናችሁ እርስ በርስ መከባበር አንዱ የአንዱን ባህል ማክበርና መረዳዳት ይጠበቅባችኋል በማለት እንደ ሀገር አስበው በጋራ ጠንክረው መማር እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) በበኩላቸው ይህ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ከሌሎቹ ለየት የሚያደርገው ከአንድ አካባቢ ሳይሆን ከመላው ኢትዮጵያ ብቃት ያላቸው ተማሪዎች ተመርጠው የሚማሩበት መሆኑ ነው ብለዋል።
በመሆኑም ተማሪዎች ነገ ይችን ሀገር ለመረከብ ጠንክረው መማር እንዳለባቸውና መምህራንም የነገ ሀገር ተረካቢ ተማሪዎችን የማብቃት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ደግሞ ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ የመጀመሪያዎቹን የ9ኛ ክፍል ተማሪዎችን ተቀብሎ ዛሬ የማስጀመሪያ ፕሮግራም በመካሄዱ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው ሰው ለማድረግ ከመምህራን ጋር በመሆን የተሰጣቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል።