News Detail

National News
Dec 20, 2025 27 views

የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ-ገዝ አድርጎ መልሶ በማቋቋም ሂደት ውስጥ ያሉ መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሄደ።

ምክክሩ በቀጣይ ራስ ገዝ ሆነው የሚቋቋሙ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ለሚያደርጉት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ግብዓት የሚሆኑ የሽግግር ረቂቅ መመሪያ ላይ ያተኮረ እንደሆነም ተመላክቷል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ መርሃ ግብሩን ባስጀመሩበት ወቅት ባስተላለፉት መልእክት በትምህርት ዘርፉ በመከናወን ላይ ያሉ የሪፎርም ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ አመራሩ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባው አብራርተዋል።
የተቋማት ስኬትም ይሁን ውድቀት በዩኒቨርሲቲው አመራርና ማህበረሰብ ላይ የሚወድቅ መሆኑን በመገንዘብ የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን በቁርጠኝነት በማስፈጸም ዩኒቨርሲቲዎች ብቃት ያለው ተወዳዳሪ የሰው ሃይል ማፍራት የሚያስችሉ ተቋማት እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባም አክለው ገልጸዋል።
በዚህም ረገድ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተጀመረውን የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ የማድረግ ሂደት የተገኙ ተሞክሮዎችና ተግዳሮቶችን በሚገባ በመለየት በመጪው አመት ራስ ገዝ ሆነው የሚቋቋሙ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገጥማቸውን ጫና በመቋቋም ለእውነትና እውቀት የቆሙና የማይገፋ ጠንካራ ተቋም ሆነው ለመውጣት አስፈላጊውን ጥረት ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሹኔ በበኩላቸው ባቀረቡት የውይይት መነሻ ሀሳብ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ራስ ገዝ አድርጎ መልሶ የማቋቋም ሂደቶችና በራስ ገዝነት የሚገኙ ቱሩፋቶችን አንስተዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባደረጉት ገለጻ ተቋማት ራስ ገዝ ሆነው ሲቋቋሙ የሀገርና የማህበረሰብ እምነትና አደራ ተጥሎባቸው መሆኑን በመረዳት የተቀመጡ ግቦችን ከስኬት ለማድረስ በጋራ መስራት እንደሚገባ አብራርተዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የአስተዳደርና መሠረተ ልማት ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ ሰለሞን አብርሃ (ዶ/ር) ለመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የራስ ገዝነት ሽግግር የተዘጋጀውን ረቂቅ መመሪያ ለውይይት መነሻ አቅርበዋል።
ረቂቅ ሰነዱ ለራስ ገዝነት ሽግግር የሚያበቁ መስፈርቶችና ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን የተካተተበት ሲሆን ዩኒቨርሲቲዎች በዚህ ረቂቅ መመሪያ እየተመዘኑ ሽግግር የሚያደርጉ በመሆኑ በተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው ማብራሪያና ምላሽ ተሠጥቶባቸዋል።
በቀጣይ ራስ ገዝ በመሆን ለሚቋቋሙ ዩኒቨርሲቲዎች ተሞክሮ እንዲሆን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የራስ ገዝነት ሽግግርን የተመለከተ የዳሰሳ ጥናት ቀርቦ ወይይት ተደርጎበታል።
Recent News
Follow Us