News Detail
Nov 11, 2025
10 views
በግሪክ ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤት ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ።
በግሪክ ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤት ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ በትምህርት ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ የግሪክ ኤምባሲ ተፈርሟል።
የመግባቢያ ስምምነት ሰነዱን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና በኢትዮጵያ የግሪክ አምባሳደር እንዲሁም ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ፈርመውታል።
በዚሁ ጊዜ የትምህርት ሚኒስትሩ በግሪክ ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤት ላለፉት ሁለት አመታት ከፍተኛ አለመግባባት ተፈጥሮ የነበረ መሆኑን አስታውሰው ይህ የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ችግሩን ሙሉ በሙሉ በመፍታት ለዜጎች ፍትሃዊና ጥራት ያለው ትምህርትን ለመስጠት ያስችላል ብለዋል።
አክለውም ኢትዮጵያና ግሪክ ለረጅም ጊዜ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አንስተው ከት/ቤቱ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን የቆየ ችግር ለመፍታትና የትምህርት ቤቱን ሌጋሲ ለማስቀጠል በትምህርት ሚኒስቴር፣ በገንዘብ ሚኒስቴር እንዲሁም እንደ መንግስት ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል።
ይህ ትምህርት ቤት የግሪክ መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር ለጥሩ ዓላማ ያቋቋመውና ለረጅም ጊዜ ሲሰራ የቆየ ትምህርት ቤት መሆኑን ገልጸው በመሃል መስመሩን ስቶ ነበር ያሉት ሚኒስትሩ አሁን የት/ቤቱን ስምና ታሪክ ባስጠበቀ መልኩ እንደገና ለማስቀጠል መንግስት ባቋቋመው ቦርድ የሚመራ የህዝብ ትምህርት ቤት እንዲሆን በጋራ ከስምምነት መደረሱን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ የግሪክ አምባሳደር አንቶኒዬስ እዝጉሮፑሎስ በበኩላቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል በባህል፣ በትምህርትና በሌሎች ዘርፎች ጠንካራ ግንኙነት እንደነበር ጠቅሰው በትምህርት ቤቱ በኩል ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት ለመፍታት ሰፊ ጊዜ የወሰደ ስኬታማ ውይይት ከተደረገ በኋላ ለዚህ ስምምነት መደረሱን ተናግረዋል።
ስምምነቱ የግሪክ ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤትን መልሶ በመቋቋም ትምህርት ቤቱ ፍትሃዊ፣ ጥራት ያለውና ተወዳዳሪ የሆኑ ተማሪዎች ያለምንም ልዩነት የሚማሩበት የትምህርት ተቋም እንዲሆን በትብብር ለመስራት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ተቀራርበው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ከዚህ ስምምነት እንዲደረስና የነበሩ አለመግባባቶች እንዲፈቱ የትምህርት ሚኒስትሩ ላደረጉት ከፍተኛ ጥረትም አምባሳደሩ አመስግነዋል።
ይህ ስምምነት የሁለቱን ሀገራት የቆየ የትምህርት ዘርፍ ትብብር በማጠናከር ረገድ ሚናው የጎላ እንደሚሆን በመድረኩ ተገልጿል።
Recent News
የፌዴራል ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተደረገላቸው አቀባበል
Dec 20, 2025
Dec 15, 2025
Nov 18, 2025